የመሬት መንሸራተቱን ተከትሎ የተለየ እንክብካቤ ለሚሹ ሕፃናት፣ነፍሰ ጡርና ለሚያጠቡ እናቶች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
የመሬት መንሸራተቱን ተከትሎ የተለየ እንክብካቤ ለሚሹ ሕፃናት፣ነፍሰ ጡርና ለሚያጠቡ እናቶች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ቀጥሏል
አርባ ምንጭ፤መጋቢት 10/2018 (ኢዜአ)፦በጋሞ ዞን በተከሰተው የመሬት መንሸራተት እና የጎርፍ አደጋን ተከትሎ ለተፈናቀሉ ወገኖች በተለይም የተለየ ትኩረትና እንክብካቤ ለሚሹ ሕፃናት፣ነፍሰ ጡርና ለሚያጠቡ እናቶች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን የክልሉ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገለጸ።
የቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ካሠች ኤልያስ እንደገለጹት በጋሞ ዞን በተከሰተ የመሬት መንሸራተትና የጎርፍ አደጋ በርካታ ወገኖች ለሞትና ለመፈናቀል የተዳረጉ ሲሆን እነዚህን ወገኖች የመደገፍ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
በአደጋው ከተፈናቀሉት መካከል የተለየ ትኩረትና እንክብካቤ የሚሹ ሕፃናት፣ ነፍሰ ጡርና የሚያጠቡ እናቶችን በልዩ ትኩረት እገዛ እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ቢሮው ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ አልሚ ምግቦችን ጨምሮ የተለያዩ የምግብና የአልባሳት ድጋፍ ማድረጉን ገልጸው፤ ድጋፉ ቀጥታ ለተጋላጭ ወገኖች እንዲደርስ በተቀናጀ መልኩ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በአደጋው ወላጆቻቸውን ያጡ ልጆችም ለስነ-ልቦና ችግር እንዳይዳረጉ በባለሙያ ጭምር የታገዘ ድጋፍና እንክብካቤ እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ከተፈናቃዮቹ መካከል ወይዘሮ ትዕግስት አጥናፉ፤ ለሕፃናትና እናቶች በተለየ መልኩ እገዛና ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ለሴቶች የንጽህና መጠበቂያዎችን ጨምሮ አልሚ ምግብ፣ ቁሳቁስና መሰል ድጋፎች እየተደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
"በአደጋው ሁለት የቤተሰብ አባላትን እንዲሁም የእርሻ ማሳ እና ቤት ንብረቴን አጥቻለሁ" ያሉት ደግሞ ከማዞ ዶይሳ ቀበሌ የተፈናቀሉት ወይዘሮ ጩናሬ ግርማ ናቸው።
ከመኝታ ፍራሽ ጀምሮ የሚያስፈልጋቸውን አልባሳት በድጋፍ እንዳገኙ ገልጸው፣ በተደረገላቸው ድጋፍና የባለሙያ እንክብካቤ እየተበረታቱና ተስፋቸው እየለመለመ መምጣቱን ተናግረዋል።
አደጋው ከደረሰበት ጊዜ አንስቶ በተለያዩ አካላት እየተደረገላቸው ያለው ድጋፍ ብርታት ስለሆናቸውም አመስግነዋል።