በአምቦ ከተማ የወጣቶች አደረጃጀቶች ለምርጫው ስኬታማነት የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአምቦ ከተማ የወጣቶች አደረጃጀቶች ለምርጫው ስኬታማነት የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ ነው
አምቦ፤መጋቢት 10/2018 (ኢዜአ) ፡-ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ አካታች፣ ነፃና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት እየተንቀሳቀሱ መሆኑን በአምቦ ከተማ የሚንቀሳቀሱ የወጣቶች አደረጃጀቶች አስታወቁ።
የምርጫው ሂደት ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የሲቪክ ማህበራት ሚና ወሳኝ በመሆኑ፣ ኢዜአ በአምቦ ከተማ ከሚንቀሳቀሱ የወጣቶች አደረጃጀቶች ጋር ቆይታ አድርጓል።
የአምቦ ከተማ ወጣቶች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ወጣት ዲቦራ ጉሉማ እንደገለጹት፤ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በዲሞክራሲያዊ መንገድ እንዲካሄድ ፌዴሬሽኑ ከቅድመ ምርጫ ዝግጅት ጀምሮ የድርሻውን እየተወጣ ይገኛል።
የመራጮች ምዝገባ ከተጀመረ አንስቶ ሂደቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲካሄድ ወጣቶችን በማስተባበር ሰፊ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
ከምርጫው በፊት የሚካሄዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክሮችና ውይይቶችን ወጣቶች በንቃት እንዲከታተሉና ጠንካራ ተሳትፎ እንዲኖራቸው እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።
ምርጫውን ከሚያስፈፅሙ አካላት ጋር ያለው ግንኙነት ጤናማ እንዲሆንና የምዝገባ ሂደቱ እንዲሳለጥ የፌዴሬሽኑ አባል ወጣቶች እስከ ቀበሌ ወርደው የማስተባበር ኃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆኑን ጠቁመዋል።
የአምቦ ከተማ ወጣቶች ማህበር ፕሬዝዳንት ወጣት ደጄነ ሀይሌ በበኩሉ፤ ምርጫው በህዝብ ዘንድ ተዓማኒነትና ቅቡልነት እንዲኖረው ማህበሩ የወጣት አደረጃጀቶችን ሚና ለማጎልበት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
“ዕድሜያቸው ለምርጫ የደረሱ ወጣቶች በመራጭነት፣ በታዛቢነትና በአስመራጭነት በንቃት እንዲሳተፉ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠርን ነው” ነው ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በከተማ አስተዳደሩ ሥር በሚገኙ ሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች የመራጮች ምዝገባ በሰላማዊ መንገድ እንዲከናወን የማህበሩ ወጣቶች ከፍተኛ እገዛ እያደረጉ መሆኑን አብራርተዋል።