የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት መርሃ ግብር በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በተግባር እያረጋገጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት መርሃ ግብር በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በተግባር እያረጋገጠ ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 10/2018 (ኢዜአ)፦ በከተሞች ተግባራዊ የተደረገው የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት መርሃ ግብር በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በተግባር እያረጋገጠ መሆኑን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ገለጸ።
የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት መርሃ ግብር በከተሞች ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ብሎም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ታስቦ የተቀረጸ ስትራቴጂካዊ ፕሮግራም ነው።
ከመርሃ ግብሩ ዋነኛ ዓላማዎችም መካከልም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች መደገፍና የስራ ዕድል መፍጠር ተጠቃሾች ናቸው፡፡
በዚህም በርካታ ዜጎችን ከተረጂነት በማላቀቅ በየሶስት ዓመቱ በምርቃት ሂደት በማሳለፍ ሃብት ፈጣሪ እንዲሆኑ ማድረግ እያስቻለ ይገኛል።
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ፈንታ ደጀን ለኢዜአ እንዳሉት፤ የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ከልማት መርሃ ግብር ጋር ተሰናስለው ተግባራዊ እየተደረጉ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት መርሃ ግብሩም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥና ወደ ሃብት ፈጣሪነት በማሸጋገር ዘመናዊ የከተሜነት ምኅዳር እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።
የመርሃ ግብሩ ተጠቃሚ ዜጎችም በከተማ ፅዳትና የአረንጓዴ ውበት የሥራ ዕድል በማመቻቸት ለከተማ ነዋሪዎች ምቹ የአኗኗር ከባቢ መፍጠር ማስቻሉንም ገልጸዋል፡፡
በዚህም የከተሞችን ውበት ማስጠበቅ፣ ዘመናዊ የከተሜነት ምኅዳር ግንባታና በከተማ ግብርና ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አስረድተዋል።
የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት መርሃ ግብሩ ከተጀመረ ወዲህ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎች ሽግግር በማድረግ መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡
በተያዘው የ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት ባለፉት ወራት ውስጥ 380 ሺህ የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት መርሃ ግብር ተጠቃሚዎችን ሽግግር ማድረጋቸውን አስረድተዋል።
በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታትም በከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት መርሃ ግብር የታቀፉ ዜጎችን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ሙሉ በሙሉ ለማሸጋገር እንደሚሰራ አንስተዋል።