ቀጥታ፡

የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ በጋሞ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች 7 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ

‎አርባ ምንጭ፤መጋቢት 10/2018 (ኢዜአ)፡- የሀገር መከላከያ ሠራዊት ልዩ ዘመቻዎች ዕዝ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች  የ7 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ።

በዕዙ የማሰልጠኛ ማዕከል አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ቦጃ አጋ ድጋፉን ዛሬ ባስረከቡበት ወቅት እንደገለጹት፣ በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች በተከሰተ አደጋ በወገኖች ላይ በደረሰ ከፍተኛ ጉዳት መላው የዕዙ አባላት ጥልቅ ሀዘን ተሰምቷቸዋል።


 

‎አባላቱ በተለያዩ ግዳጆችና ሌሎች ተግባራት ላይ ቢሆኑም ባሉበት ሆነው ገንዘብ በማዋጣት ለጋሞ ህዝብ ያላቸውን አጋርነት ለማሳየት  ዛሬ የ7 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

‎ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋምና ለዘላቂ መፍትሄ በሚደረገው ጥረትም የዕዙ አባላት ከዞኑ አስተዳደር ጎን እንደሚቆሙ አረጋግጠዋል።

‎ለተጎጂዎች የቀረበውን ድጋፍ የተረከቡት የጋሞ ዞን የመንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ ተመስገን ኢዩኤል በበኩላቸው፥ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ቀዳሚ ተግባሩ የሀገር ሉአላዊነትን ማስከበር ቢሆንም የዕዙ አባላት በዞኑ የተጎዱ ወገኖችን ለመደገፍ ላሳዩት ቁርጠኝነት አመስግነዋል።


 

‎ከሀገር ውስጥና ከውጭ በተለያዩ አካላት እየተደረገ ያለው ድጋፍና አለኝታነትን የማረጋገጥ ተግባር ተጎጂዎችን ብሎም የዞኑ ህዝብና አስተዳደር እንዲጽናኑ እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም