ቀጥታ፡

በአካባቢው የተገኘውን ሰላም በማጽናት የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን እናስቀጥላለን - የጉሊሶ ከተማ ነዋሪዎች

ጉሊሶ፤ መጋቢት 10/2018 (ኢዜአ):-በምዕራብ ወለጋ ዞን የጉሊሶ ከተማ ነዋሪዎች በአካባቢያቸው ሰላምን በማስፈን የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ገለጹ።

ከከተማዋ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በልማት፣ በሰላም እና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።  


 

በውይይቱ ላይ የተሳተፉ ነዋሪዎች እንደገለጹት፤ በአካባቢያቸው እየተከናወኑ ያሉ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ ቅድሚያ ለሰላም መስፈን ትኩረት ሊሰጥ ይገባል።   

ቀደም ሲል የነበሩ የፀጥታና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በህዝቡና በፀጥታ አካላት የተቀናጀ ጥረት እየተፈቱ መሆኑን ተናግረዋል።   


 

የጉሊሶ ከተማ ነዋሪ ሸህ አብዱ ሀሰን፣ "የአካባቢውን ሰላም በማፅናት የልማት ሥራዎችን ለማስቀጠል የድርሻችንን እንወጣለን" ብለዋል።   

ለዚህም የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመተባበር የሚያደርጉትን ጥረት  እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል።   

ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ተክሌ ሞሲሳ፤ በአሁኑ ወቅት በህዝቡና በፀጥታ አካላት ቅንጅት በአካባቢው አስተማማኝ ሰላም መስፈኑን ጠቅሰዋል።   


 

የተገኘው ለውጥ እንዲቀጥል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ትብብራችንን እናጠናክራለን ሲሉም ገልጸዋል።

መድረኩን የመሩት የምዕራብ ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተሊላ ተረፋ፤ ባለፉት ዓመታት በዞኑ አጋጥሞ የነበረው የፀጥታ ችግር የልማት ሥራዎች በሚፈለገው ፍጥነትና ጥራት እንዳይከናወኑ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን አስታውሰዋል።   


 

አሁን ላይ በህብረተሰቡና በፀጥታ አካላት ጥምረት ሰላም እየሰፈነ ሲሆን የልማት ስራዎችም በስፋት እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።   

ይህ ውጤት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ህብረተሰቡ ሰላምን በመጠበቅ ለልማት ሥራዎች ስኬታማነት የሚያደርገውን ርብርብ እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም