ኢትዮጵያ የሴቶችን ውሳኔ ሰጪነት ለማረጋገጥ የፈጠረችው ምቹ ምኅዳር በምሳሌነት የሚወሰድ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የሴቶችን ውሳኔ ሰጪነት ለማረጋገጥ የፈጠረችው ምቹ ምኅዳር በምሳሌነት የሚወሰድ ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 10/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የሴቶችን ውሳኔ ሰጪነት ለማረጋገጥ የፈጠረችው ምቹ ምኅዳር በምሳሌነት የሚወሰድ መሆኑን የአፍሪካ ሕብረት የሴቶች፣ የሰላምና ደኅንነት ልዩ ልዑክ አምባሳደር ላይቤራታ ሙላሙላ ገለጹ።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ግንቦት 24/2018 ዓ.ም ድምፅ በሚሰጥበት የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ከየካቲት 28/2018 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል።
መራጮችም "ምርጫዬ" በተሰኘ የዲጂታል መተግበሪያና በየምርጫ ጣቢያዎች በአካል በመገኘት ድምፅ መስጠት የሚያስቻለቸውን የምርጫ ካርድ በመውሰድ ላይ ናቸው።
በዘንድሮው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫም 47 ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች 10ሺህ 934 ዕጩዎችን በማስመዝገብ በመገናኛ ብዙኅን አማካኝነት የምርጫ መወዳደሪያ የፖሊሲ አማራጫቸውን እያስተዋወቁ ይገኛሉ።
አምባሳደር ላይቤራታ ሙላሙላ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የአፍሪካ ሕብረት አባል ሀገራት ሀገራዊ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሕዊና ሰላማዊ መሆኑን ለማረጋገጥ የምርጫ ታዛቢ ቡድን እንደሚያሰማራ ገልጸዋል።
በአህጉሪቱ ለሚካሄዱ ሀገራዊ የምርጫ ሂደቶች ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሕዊና አካታችነትም የሴቶች የነቃ ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
ለዚህም የአፍሪካ ሕብረት የሴቶች፣ የሰላምና ደኅንነት ልዩ ልዑክ የአህጉሪቱ ሴቶች በምርጫ ወቅት የመምረጥና መመረጥ መብታቸውን እንዲጠቀሙ የማበረታቻ ድጋፍ እንደሚያደርጉ አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በሚቀጥለው ግንቦት ወር የምታካሂደው 7ኛ ጠቅላላ ምርጫም ነፃ፣ ፍትሕዊና አካታችነት ለማረጋገጥ ገንቢ ሚና እንደሚወጡ አስታውቀዋል።
በአፍሪካ አብዛኛውን የማህበረሰብ ክፍል የሚሸፍኑት ሴቶች መሆናቸውን አንስተው፤ ሀገራት በሚያካሂዱት ሀገራዊ ምርጫዎች ሴቶች የመምረጥና መመረጥ መብታቸውን መጠቀም ይኖርባቸዋል ብለዋል።
በምርጫ ዴሞክራሲያዊነት የሚኖር የሴቶች ተሳትፎ የአመራር ድርሻና የፖለቲካ ውክልናን እንደሚያረጋግጥም አብራርተዋል።
ሴቶች በፖለቲካ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስክ ዕድላቸውን መጠቀም ከቻሉ ለማህበረሰብ ለውጥ ወሳኝ መሆናቸውን አምባሳደሯ ያለፉበትን የተሞክሮ መንገድ በአብነት ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት የሴቶችን ውሳኔ ሰጪነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የፈጠረው ምቹ ምኅዳር በምሳሌነት የሚወሰድ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
በሚቀጥለው ግንቦት 24/2018 ዓ.ም ድምፅ በሚሰጥበት 7ኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ ሴቶች ትርጉም ባለው መልኩ የመምረጥና መመረጥ መብታቸውን የሚጠቀሙበት ወሳኝ ዕድል እንደሆነ ተናግረዋል።