ቀጥታ፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ለዒድ አል ፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 10/2018(ኢዜአ)፦ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ለዒድ አል ፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለዒድ አል ፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት የዒድ አል ፈጥር በዓል፣ በመተባበር የደስታ ብርሃን የሚንፀባረቅበት ሕይወት በበጎነት የምትደምቅበት ታላቅ ዕለት ነው ብለዋል።

በታላቁ የረመዳን ወር ጾሙ ከእምነቱ በተሻገረ አስተሳስቦናል፤ ሶላቱ አቀራርቦናል፤ ኢፍጣሩ በአንድ ማዕድ ዙሪያ ሲያሰባስበን ከርሟል፤ ኢትዮጵያዊ አብሮነታችንን በተግባር አሳይቷል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ለሰው ልጆች ሁሉ ጠቃሚ የሆኑት የዒድ አል ፈጥር ዕሴቶች ለሀገር ግንባታ አስፈላጊ ዕሴቶች ናቸው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በታላቁ የጾም ወቅት የተጀመረውን ኅብረት እና መተዛዘን ዘላቂነቱን ማስቀጠል እንደሚገባ አመልክተዋል።

በታሪክ ሁሉ እንዳየነው ሀገር ያለ አብሮነት እና ያለ በጎነት ልትገነባ አትችልም፡፡ የበጎነት እጆች ችግርን ወደ ተስፋ፤ እንባን ወደ ሳቅ ይቀይራሉና ለበጎነት መበርታት ያስፈልጋል ሲሉም ገልጸዋል።

ኅብረ ብሔራዊ ለሆነችው ኢትዮጵያ መቻቻል እና በልዩነት ውስጥ ያለውን ውበት ጌጥ አድርጎ በዓለም ሁሉ ፊት መድመቅ ለነገይቱ ኢትዮጵያ ብሩህ ተስፋን የሚሰንቅ እንደሆነም ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ የልማት ጉዞ ዘላቂ እንዲሆን፣ ዜጎችንም ፍትሐዊ ተጠቃሚ እንዲያደርግ ሁላችንም ለሀገራችን የምንችለውን ሁሉ እናድርግ ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም