ሊቨርፑል ባየር ሙኒክ እና አትሌቲኮ ማድሪድ ለሩብ ፍጻሜ አለፉ - ኢዜአ አማርኛ
ሊቨርፑል ባየር ሙኒክ እና አትሌቲኮ ማድሪድ ለሩብ ፍጻሜ አለፉ
አዲስን አበባ፤ መጋቢት 10/2018 (ኢዜአ)፦ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ሶስት የጥሎ ማለፍ የመልስ ጨዋታዎች ማምሻውን ተደርገዋል።
በአንፊልድ ሮድ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ሊቨርፑል ጋላታሳራይን 4 ለ 0 ረቷል።
ዶምኒክ ስቦዝላይ፣ ሁጎ ኢኪቲኬ፣ ራያን ግራቨንበርች እና መሐመድ ሳላህ ግቦቹን አስቆጥረዋል።
ሊቨርፑል በደርሶ መልስ ውጤት 4 ለ 1 በማሸነፍ ሩብ ፍጻሜውን ተቀላቅሏል።
በሌላኛው መርሐ ግብር ባየር ሙኒክ አትላንታን 4 ለ 1 አሸንፏል።
በአሊያንዝ አሬና ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ሃሪ ኬን በጨዋታ እና ፍጹም ቅጣት ምት ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ሌናርት ካርል እና ሉዊስ ዲያዝ ቀሪዎቹን ጎሎች ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
ላዛር ሳማርድዚች ለአትላንታ ብቸኛውን ጎል አስቆጥሯል።
የጀርመኑ ባየር ሙኒክ በአጠቃላይ ውጤት 1ዐ ለ 2 በማሸነፍ ሩብ ፍጻሜ ገብቷል።
በቶተንሃም ሆትስፐርስ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ቶተንሃም ሆትስፐርስ አትሌቲኮ ማድሪድን 3 ለ 2 አሸንፏል።
ዣቪ ሲመንስ በጨዋታ እና በፍጹም ቅጣት ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ራንዳል ኮሎ ሙዋኒ ቀሪዋን ጎል ከመረብ ጋር አገናኝቷል።
ጁሊያን አልቫሬዝ እና ዴቪድ ሃንኮ ለአትሌቲኮ ማድሪድ ግቦቹን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
አትሌቲኮ ማድሪድ በድምር ውጤት 7 ለ 5 በማሸነፍ ሩብ ፍጻሜ ገብቷል።
ዛሬ አስቀድሞ በተደረገ ጨዋታ ባርሴሎና ኒውካስትል ዩናይትድን 7 ለ 2 በማሸነፍ በድምር ውጤት 8 ለ 3 በመርታት ሩብ ፍጻሜውን ተቀላቅሏል።
ጨዋታዎቹን ተከትሎ ሩብ ፍጻሜ የገቡ ስምንት ክለቦች ተለይተዋል።
በዚሁ መሰረት ሪያል ማድሪድ ከባየር ሙኒክ፣ ባርሴሎና ከአትሌቲኮ ማድሪድ፣ ፒኤስጂ ከሊቨርፑል እና ስፖርቲንግ ሊዝበን ከአርሰናል በሩብ ፍጻሜው ይጫወታሉ።
የሩብ ፍጻሜ የመጀመሪያ ዙር መጋቢት 29 እና 30 እንዲሁም ሚያዚያ 6 እና 7 ቀን 2018 ዓ.ም የመልስ ጨዋታዎች ይደረጋሉ።