ኢትዮጵያ ከንግድ አበዳሪዎች ጋር ለምታደርገው ድርድር ውጤታማነት የቻይና ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቀረበች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከንግድ አበዳሪዎች ጋር ለምታደርገው ድርድር ውጤታማነት የቻይና ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቀረበች
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 9/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ከንግድ አበዳሪዎች ጋር የምታደርገውን ድርድር ለማጠናቀቅ በምታደርገው ጥረት የቻይና ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ጥሪ አቀረቡ።
የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቼን ሃይ እና ከቻይና ኤክስፖርት-ኢምፖርት ባንክ (China Exim Bank) የልዑካን ቡድን ጋር በጋራ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
ውይይቱ በዋናነት ትኩረቱን ያደረገው በቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ላይ ሊኖሩ በሚችሉ የገንዘብ ድጋፍ አማራጮች ዙሪያ ነው።
በተጨማሪም፣ በኢትዮጵያ የቡድን 20 (G20) የጋራ ማዕቀፍ የዕዳ ሽግሽግ (debt restructuring) ሂደት አስመልክቶ በሁለቱ ወገኖች መካከል ምክክር ተደርጓል።
ሚኒስትር አህመድ ሽዴ፣ ቻይና የአበዳሪዎች ኮሚቴ (OCC) ሰብሳቢ በመሆን ላሳየችው አመራርና በዕዳ ሽግሽግ ሂደቱ ወቅት ላደረገችው ገንቢ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
ሂደቱ አሁን ላይ በመጨረሻው ምዕራፍ ላይ የሚገኝ በመሆኑ፣ የተጀመረውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ መቀጠል አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል።
አያይዘውም፣ ኢትዮጵያ ከንግድ አበዳሪዎች(commercial creditors) ጋር የምታደርገውን ድርድር በማጠናቀቅ በኩል የቻይና ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ማቅረባቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መረጃ አመላክቷል።