ጣልያን በማቴይ እቅድ የኢትዮጵያን ስትራቴጂካዊ መሰረተ ልማቶች ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኗን ገለጸች - ኢዜአ አማርኛ
ጣልያን በማቴይ እቅድ የኢትዮጵያን ስትራቴጂካዊ መሰረተ ልማቶች ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኗን ገለጸች
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 9 /2018 (ኢዜአ)፦ ጣልያን የኮይሻ ኃይል ማመንጫን ጨምሮ በማቴይ እቅድ (Mattei Plan) የኢትዮጵያን ስትራቴጂካዊ መሰረተ ልማቶች ለመደገፍ ጽኑ ፍላጎት እና ቁርጠኝነት እንዳላት አስታወቀች።
በገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ የተመራው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በስትራቴጂካዊ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ዙሪያ ከጣልያኑ የማቴይ ዕቅድ (Mattei Plan) ግብረ ኃይል ጋር በሮም ውይይት አድርጓል።
ውይይቱ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ትብብር ይበልጥ ለማሳደግ ያለመ ሲሆን በኢትዮጵያ የልማት አጀንዳ ውስጥ ቁልፍ ድርሻ ባላቸው ትላልቅ ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት አድርጓል።
ፕሮጀክቶቹ የኮይሻ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ የግንባታ ፕሮጀክት እና የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ልማት ናቸው።
እነዚህ ግዙፍ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን የኢነርጂ አቅም እና የአቪዬሽን መሠረተ ልማት በማዘመን ረገድ ከፍተኛ ለውጥ እንደሚያመጡና ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገትን እንደሚደግፉ ታምኖበታል።
በውይይቱ ላይ የጣልያን ወገን በማቴይ እቅድ ጥላ ሥር ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለማጠናከር ያለውን ጽኑ ቁርጠኝነት ገልጿል።
ይህም ፈጠራ የታከለባቸው የፋይናንስ ዘዴዎችን በመጠቀም እና በመንግሥትና በግል ዘርፍ መካከል ያለውን ትብብር በማጠናከር ተግባራዊ እንደሚሆን ተመልክቷል።
በውይይቱ የተሳተፈው የጣልያን ግብረ ኃይል ከጣልያን የኢኮኖሚና ፋይናንስ ሚኒስቴር፣ ከውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስቴር፣ የጣልያን የኤክስፖርት ክሬዲት ኤጀንሲ (SACE)፣ የጣልያን መንግስት የፋይናንስ ተቋም (CDP) እና የጣልያኑ የግንባታ ኩባንያ ዊ ቢውልድ ግሩፕ (Webuild Group) የተወጣጡ ከፍተኛ ተወካዮችን ያካተተ ነው።
በውይይቱ ወቅት ሁለቱ ወገኖች ለኮይሻ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ፕሮጀክት የሚያስፈልገውን የፋይናንስ ዝግጅት፣ ተጨማሪ ሀብትን ማሰባሰብ እና የፋይናንስ መዋቅሩን ማሳለጥ በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ መክረዋል።
በተጨማሪም ለቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት የተቀናጀ የፋይናንስ አማራጮችን (blended finance) በመጠቀም የግል ዘርፉን ተሳትፎ ማሳደግ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ሰፊ ሃሳብ ተለዋውጠዋል።
የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ፕሮጀክቶቹ በአገሪቱ እየተከናወነ ያለውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እና የረዥም ጊዜ የልማት ግቦችን ለመደገፍ ያላቸውን አስፈላጊነት አስገንዝበዋል።
ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ጣልያን ለኢትዮጵያ እያደረገች ላለው ቀጣይነት ያለው አጋርነት እና ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ሁለቱም ወገኖች የፕሮጀክቶቹን ግንባታ ለማፋጠን እና የተገቡ ቃሎችን ወደ ተጨባጭ ውጤት ለመቀየር በቴክኒክ ረገድ በቅርበት አብሮ ለመሥራት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መረጃ አመልክቷል።