ቀጥታ፡

በአማራ ክልል የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ የሕዝብ እርካታን ለማረጋገጥ የተጀመረው ስራ ይጠናከራል

ባሕር ዳር፤መጋቢት 9/2018 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ዘመኑን በሚመጥን መልኩ በቴክኖሎጂ ታግዞ ተደራሽ እንዲሆን የተጀመሩ ስራዎች እንደሚጠናከሩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ገለጹ።

''ዲጂታል ሲቪል ሰርቪስ ለኢትዮጵያ ከፍታ'' በሚል መሪ ሀሳብ የክልሉ የመንግሥት አገልግሎት እና አስተዳደር ሪፎርም ፍኖተ ካርታ ትውውቅ መድረክ በባሕር ዳር ከተማ ተካሄዷል።


 

ፍኖተ ካርታው በክልሉ የሚገኙ የመንግሥት ተቋማትን አገልግሎት አሰጣጥ ተደራሽ፣ ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል ሥርዓት ለመዘርጋት ያለመ መሆኑም ተመልክቷል።

ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በመድረኩ ላይ እንዳሉት፤ በየጊዜው እያደገ የመጣውን የሕዝብ የመገልገል ፍላጎት መሠረት ያደረገ ቀልጣፋ አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ የመንግሥት ቀዳሚ ተግባር ነው። 

ፍኖታ ካርታው በክልሉ የመንግሥት ሠራተኞች የብቃት ምዘና ሥርዓትን በመገንባት ውጤታማ አገልግሎት አሰጣጥን ለማረጋገጥ ያግዛል።

በተጨማሪም የመንግስት ሰራተኛውን የማስፈጸም አቅም ማሳደግ፣ ብዝሃነትንና አካታችነትን ያረጋገጠ ሲቪል ሰርቪስ መገንባት እንዲሁም ነፃ፣ ገለልተኛና ዲጂታል የሥራ አካባቢን መፍጠር ዋና ዋና የሪፎርሙ አቅጣጫዎች መሆናቸውን አስረድተዋል።

ተቋማትም ፍኖተ ካርታውን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የአገልግሎት ጥራትን፣ ፍጥነትን፣ ፍትሐዊነትንና እርካታን በሚያረጋግጥ መልኩ ሊሠሩ እንደሚገባም አሳስበዋል።

ለዚህም ሲቪል ሰርቫንቱ የዘመኑን ቴክኖሎጂ በመታጠቅ፣ በላቀ ብቃት፣ ዕውቀትና ክህሎት ታግዞ ሪፎርሙን ሊተገብር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።


 

የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ሀገራዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥና ኢትዮጵያን ለማሻገር የሚያስችል የሲቪል ሰርቪስ ፖሊሲ ተቀርጾ ወደ ትግበራ መገባቱን ገልጸዋል። 

ፖሊሲው ሀገራዊ ዕውቀትንና ልምድን መሠረት ያደረገ በመሆኑ በፍጥነት ለውጥ ለማስመዝገብ እንደሚያስችል ጠቁመዋል።

የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን በ36 ማዕከላት መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መጀመሩን የጠቀሱት ኮሚሽነሩ፤ ይህም ቴክኖሎጂን በመጠቀም የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት እያስቻለ መሆኑን አስረድተዋል።

የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ባንችአምላክ ገብረማርያም በበኩላቸው፤ ሪፎርሙ ቀደም ሲል በተቋማት ይስተዋሉ የነበሩ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።


 

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተግባራዊ በተደረገባቸው ከተሞች የሕዝብ እርካታን 97 በመቶ ማድረስ መቻሉን የገለጹት ኃላፊዋ፤ ይህንን ውጤት ለማስፋት የሪፎርም ፍኖተ ካርታውን በላቀ ትብብር መተግበር እንደሚገባም አሳስበዋል።

በመድረኩ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን፤ በመጀመሪያው ምዕራፍ ወደ ትግበራ ከሚገቡ የተለያዩ የክልል ተቋማት ጋር የሰነድ ርክክብ ተከናውኗል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም