የኢድ አልፈጥር በዓልን የተቸገሩትን በመርዳት ለማክበር ተዘጋጅተናል-የእስልምና እምነት ተከታዮች - ኢዜአ አማርኛ
የኢድ አልፈጥር በዓልን የተቸገሩትን በመርዳት ለማክበር ተዘጋጅተናል-የእስልምና እምነት ተከታዮች
ቦንጋና ሚዛን፤መጋቢት 9/2018 (ኢዜአ)፦የኢድ አልፈጥር በዓልን የተቸገሩትን በመርዳት፤ በአብሮነትና በመደጋገፍ ለማክበር መዘጋጀታቸውን የቦንጋና የሚዛን አማን ከተሞች የእምነቱ ተከታዮች ገለፁ።
የኢድ አፈጥር በዓል በሕዝበ ሙስሊሙ ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠውና ከአንድ ወር የፆም ቆይታ በኋላ የሚከበር በዓል ነው።
ይህን አስመልክቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው የቦንጋና የሚዛን አማን ከተሞች የእምነቱ ተከታዮች እንዳሉት፤ የኢድ አልፈጥር በዓል የአብሮነትና የመደጋገፍ ባህል ጎልቶ የሚታይበት በዓል መሆኑን ተናግረዋል።
የፆሙ ወቅት ለሀገር ዱአ በማድረግ፣ በመስገድና በተለያዩ ሀይማኖታዊ ስርዓቶች በጥሩ ሁኔታ ማለፉንም ተናግረዋል።
የቦንጋ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ ራህመት መሐመድ፤ የኢድ አፈጥር በዓል በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በጉጉት የሚጠበቅ መሆኑን በመግለጽ እርስ በእርስ በመጠያየቅ አብሮ በመብላትና በመጠጣት በደስታና በሰላም እንደሚያሳልፉ ተናግረዋል።
የኢድ አፈጥር በዓልን ከሌሎች ሰዎች ጋር አብሮ ለማክበር መዘጋጀቱን ወጣት መሐመድ አሊ አብራርቷል።
በዓሉ ያለው ከሌለው ጋር ተካፍሎ በደስታና በመተሳሰብ እንደሚከበርም ተናግሯል።
በዓሉን ከዘመድ ጋር ከሚያደርጉት መጠያየቅ ባለፈ ከሌላ እምነት ተከታዮች ጋርም ያለምንም ልዩነት በአብሮነት እንደሚያከብሩም ገልፀዋል።
የቤንች ሸኮ ዞን እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ሰብሳቢ ሼህ አሊ ዑመር እንዳሉት፤ የዒድ ደስታን የጋራ ለማድረግ ከጎረቤት ጋር ማክበር ይገባል።
የዒድ አል ፈጥር በዓልን የእምነቱ አስተምህሮ በሚያዘው መሠረት አቅመ ደካሞችን በመጠየቅ፣ በመከባበር እና በመተጋገዝ መንፈስ በማክበር አብሮነትን ማጎልበት እንደሚገባ ገልጸዋል።
ለሰው ልጆች ሁሉ መልካም ማድረግ የቁርዓን መልእክት መሆኑን ጠቅሰው በረመዳን ወር የተፈጸሙ ሰውኛ ተግባራትን በሌሎችም ጊዜያትም መፈጸም ከሕዝበ ሙስሊሙ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።
የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪ አቶ በረከት አደም፤ ዒድ ሙሉ ደስታን የሚፈጥርልን ከተቸገሩት ጋር አብረን በዓሉን ስናከብር ነው ሲሉ ገልጸዋል።
በረመዳን ወር ስናደርገው የቆየነውን አቅመ ደካማ ወገኖችን የመጠየቅ ተግባርን ማስቀጠል አለብን ያሉት ደግሞ አቶ አደም አባስመል ናቸው።
መምህር መሐመድ ሰይድ የተባሉ ሌላው የከተማዋ ነዋሪ በበኩላቸው መተሳሰብ ያለ የነበረ ባህላችን በመሆኑ በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ወገኖችን በማገዝ በዓሉን እናሳልፋለን ብለዋል።