ቀጥታ፡

በጠቅላላ ምርጫው የዞኑን የመልማት ጸጋዎች በመለየት አማራጭ ሃሳቦችን ይዘን ቀርበናል- የፖለቲካ ፓርቲዎች

ዲላ ፤መጋቢት 9/2018((ኢዜአ) :- በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የዞኑን የመልማት ጸጋዎች በመለየት አማራጭ ሃሳቦችን ይዘው መቅረባቸውን በጌዴኦ ዞን የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።

በቀጣይ ግንቦት 24 በሚካሔደው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ በዞኑ ብልጽግና ፓርቲ፣ ጌህዴድ፣ ኢዜማና ነዕፓን ጨምሮ ሌሎችም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ እያደረጉ ይገኛል። 

ተፎካካሪ ፓርቲዎቹ እንደገለፁት፤ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የዞኑን የመልማት ጸጋዎች በመለየት አማራጭ ሃሳቦችን ይዘው ቀርበዋል።

ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የጌዴኦ ዞን ሴቶች ክንፍ ሃላፊ ወይንሸት በዛብህ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ አሳታፊ፣ ነጻና ገለልተኛ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በቁርጠኝነት እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ጌዴኦ በሃገር በቀል እውቀቱ አካባቢውን መጠበቅ የኑሮው መሰረቱ መሆኑን አንስተው ይህም ጎልቶ እንዲወጣና የአርሶ አደሩን ኑሮ እንዲያሻሽል በማኒፌስቷቸው በግልጽ ለይተው ለመወዳደር እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በምርጫው በሰላማዊ መንገድ ከመሳተፍ ባለፈ የዞኑን የመልማት ጸጋዎችን በመለየት አማራጭ ሀሳቦችን ይዘው መቅረባቸውን ያነሱት ደግሞ የጌዴኦ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ዋና ጸሐፊ ግርማ ሐጌ ናቸው።

ዞኑ በጥምር ግብርናና በተለያዩ እጽዋቶች የተዋበ በመሆኑ ከእርሻ ልማት ውጭ በሆኑ የግብርና ልማት ሥራዎች በተለይ በንብ ማነብ ረገድ ያለውን አቅም መጠቀም እንደሚገባ ተናግረዋል።

በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዞኑ የሚታወቅበትን የአካባቢ ጥበቃ ጸጋ እንዲጎለብት ለማድረግ በማኒፌስቷቸው አካተው ለመወደደር መቅረባቸውን ገልጸዋል።

የጌዴኦ ዞን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢና የህብር ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ የዞኑ ተወካይ አቶ መስከረም ተዘራ በበኩላቸው የዞኑ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ‎በጋራ ምክር ቤቱ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ በቅንጅት እየሰራን ነው ብለዋል።

የጋራ ምክር ቤቱ ፓርቲዎች የተሻለ ሃሳብ ለህዝብ እንዲያቀርቡ ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር የበኩሉን ኃላፊነት እየተወጣ  መሆኑን አስረድተዋል።

በፓርቲ ደረጃ ያለ ዘላቂ ሰላምና ብሔራዊ መግባባት የሚመጣ እድገት የለም የሚል ጽኑ አቋም ይዘው እየሰሩ መሆናቸውን  አቶ መስከረም አንስተዋል።

በተለይ በዞኑ ለሰላም እሴት መጎልበት ትልቅ ድርሻ ያላቸው ባህላዊ እሴቶች እንዲተዋወቁ በማኒፌስቷቸው ለይተው እየሰሩ መሆኑንም አክለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም