የኢትዮጵያ ባንኮችንና በኢንዱስትሪ ዞኖች የሚያለሙ ባለሃብቶችን ትብብር የሚያጎለብት መመሪያ ተግባራዊ ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ባንኮችንና በኢንዱስትሪ ዞኖች የሚያለሙ ባለሃብቶችን ትብብር የሚያጎለብት መመሪያ ተግባራዊ ተደርጓል
አዲስ አበባ፤መጋቢት 9/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የግልና የመንግስት ባንኮችንና የኢንዱስትሪ ዞን አልሚ ባለሃብቶችን የወጪ ንግድና ተኪ ምርት አቅም የሚያሳድግ የትብብር መመሪያ ተግባራዊ መደረጉን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ገለጸ።
የፋይናንስ ተቋማት በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ የሚኖራቸውን ተሳትፎ ማጠናከር የሚያስችል የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
በመድረኩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኦፕሬሽንና ፓርክ አስተዳደር ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍጹም ከተማ እንዳሉት፤ ባለፉት ዓመታት ከ1 ነጥብ 5 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ የኢንቨስትመንት ፍሰትን የሚያሳልጥ የኢንዱስትሪ ዞኖች ተገንብተዋል።
በአሁኑ ወቅትም የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን 11 ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችን፣ ሁለት መካከለኛ ኢንዱስትሪ ፓርኮችንና አንድ የአይ.ሲ.ቲ ፓርክን እያስተዳደረ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ቀደም ባሉት ዓመታት በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ዞኖች የተሰማሩ ባለሃብቶች አብዛኞቹ ከውጭ የመጡ እንደነበር አስታውሰዋል።
የሀገር ውስጥ አልሚ ባለሃብቶችን ለማበረታታት በተከናወኑ ተግባራት አሁን ላይ በኢንዱስትሪ ዞኖች ከተሰማሩ 250 ባለሃብቶች ውስጥ 65 በመቶ የሚሆኑት የሀገር ውስጥ አልሚዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።
የሀገር ውስጥ አልሚ ባለሃብቶች የኢንዱስትሪ ዞኖች የተሟላላቸውን መሰረተ ልማቶች በመጠቀም ማልማት የሚችሉበትን አቅም እያሳደጉ መሆኑንም አስረድተዋል።
የሀገር ውስጥ ባለሃብቶችን ምርታማነት ለማስቀጠል መሰረተ ልማት፣ የፋይናንስ አቅርቦትና ተወዳዳሪነትን የሚያስቀጥልና ጊዜ ቆጣቢ የፋይናንስ ሥርዓት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ለዚህም በልዩ የኢኮኖሚ ዞን አዋጁ በኢንዱስትሪ ዞኖች የሚያለሙ ባለሃብቶችና ሁሉም ባንኮች መስፈርቱን አሟልተው በትብብር መሥራት የሚያስችል ዕድል መፍጠር እንደተቻለ አንስተዋል።
የውጭ ባለሃብቶች የራሳቸውን ካፒታል ይዘው እንደሚመጡ ገልጸው፤ የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ግን በባንኮች ሊደገፉ ይገባል ነው ያሉት፡፡
ከዚህ ቀደም በኢንዱስትሪ ዞኖች አገልግሎት መስጠት የሚችለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻ እንደነበር አስታወሰው፤ መመሪያው አቅም የላቸው ባንኮች መስፈርቱን አሟልተው መግባት እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል፡፡
የልዩ ኢኮኖሚ ዞን አዋጁና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመሪያ የግልና የመንግሥት ባንኮችንና በኢንዱስትሪ ዞኖች የሚያለሙ ባለሃብቶችን ትብብር እንደሚያጎለብት ተናግረዋል።
በኢንዱስትሪ ዞኖች እያለሙ ያሉ ባለሃብቶችና ባንኮች የምርታማነትንና የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያስቀጥል ጠንካራ ትብብር መገንባት እንዳለባቸው ጠቅሰዋል።
የኢንዱስትሪ ዞኖች በተኪና ወጪ ንግድ ምርት፣ በሥራ ዕድልና ቴክኖሎጂ ሽግግር የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ለማጎልበት የትብብር አቅምን ማሳደግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።