ህዝበ ሙስሊሙ የኢድ አልፈጥር በዓልን ሲያከብር የተቸገሩ ወገኖችን በመጠየቅና በመረዳዳት ሊሆን ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ህዝበ ሙስሊሙ የኢድ አልፈጥር በዓልን ሲያከብር የተቸገሩ ወገኖችን በመጠየቅና በመረዳዳት ሊሆን ይገባል
አዲስ አበባ፤መጋቢት 9/2018 (ኢዜአ)፦ህዝበ ሙስሊሙ የኢድ አልፈጥር በዓልን ሲያከብር የተቸገሩ ወገኖችን በመጠየቅና በመረዳዳት ሊሆን እንደሚገባ የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሸይኽ ሙሐመድ ሸሪፍ ገለጹ ።
የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የኢድ አልፈጥር በዓልን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
በመግለጫውም በዓሉ በአዲስ አበባ ስታዲየም እና በሌሎች አካባቢዎች እንደሚከበር ተገልጿል።
የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሼይኸ መሀመድ ሸሪፍ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በረመዳን ወር የታየው መንፈሳዊ ጥንካሬ፣ መተባበር እና መደጋገፍ በበዓሉ ዕለትም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።
በጾሙ ወቅት የነበረው የመረዳዳት ባህል ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ጠቅሰው፤ በተለይም አቅመ ደካሞችንና የተቸገሩ ወገኖችን በማሰብ በዓሉን በጋራ ማክበር ያስፈልጋል ብለዋል ።
ህዝበ ሙስሊሙ በረመዳን ጾም ወቅት ካለው ላይ በማካፈል፣በመረዳዳትና በመተጋገዝ በረከት ሲያገኝ እንደቆየ ሁሉ የመጠያየቅና የመረዳዳት እሴት ሁልጊዜም አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል፡፡