ቀጥታ፡

ጠቅላላ ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ተዓማኒነት ያለው ሆኖ በስኬት እንዲጠናቀቅ የድርሻችን እንወጣለን - ሲቪክ ማህበራት

ሰቆጣ፤ መጋቢት9/2018 (ኢዜአ) ፡-የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ተዓማኒነት ያለው ሆኖ በስኬት እንዲጠናቀቅ የድርሻችን እንወጣለን ሲሉ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የሚገኙ የሲቪክ ማህበራት ገለፁ።

ኢትዮጵያ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለማከናወን የቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ ትግበራ ላይ ትገኛለች።

ጠቅላላ ምርጫው ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊ፣ አሳታፊና ተዓማኒነት ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅ የሲቪክ ማህበራት ሚና የላቀ መሆኑ ይታወቃል።

የሲቪክ ማህበራቱ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለመራጭነት የሚያበቃቸውን ካርድ በማውጣትና የታዛቢነት ሚናቸውን ለመወጣት እያደረጉት ያለውን ዝግጅት አስመልክቶ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

የአማራ ወጣቶች ማህበር የዋግ ኽምራ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ሃላፊ ወጣት ወንድሙ ገብረ እግዚአብሄር እንደገለጸው የማህበሩ አባላት የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ እየሰሩ ነው።

የማህበሩ አባላት ከወገኝተኝነት በፀዳ መልኩ በሰላም ማስጠበቅና ምርጫው ሰላማዊ ፍትሃዊና ተዓማኒነት ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅ በቁርጠኝነት እየሰሩ እንደሚገኝ ገልጿል።

የክልሉ ወጣቶች ማህበርና የፌደራል ወጣቶች ካውንስል ለማህበሩ በሰጡት ውክልና መሰረትም 170 ወጣቶች በታዛቢነት ለማሳተፍ የልየታ ስራ ማከናወናቸውን አስረድቷል።

በታዛቢነት ለተለዩ የማህበሩ አባላት ስልጠና ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን ጠቁመው በስልጠናው በሚያገኙት እውቀትና ባላቸው ልምድ በመጠቀም ለምርጫው ስኬት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግሯል።

ወጣቱ የመራጭነት ካርድ በማውጣት በምርጫው የሚኖረውን ተሳትፎ የበለጠ እንዲያሳድግ ማህበሩ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አመልክቷል።

የብሔረሰብ አስተዳደሩ መምህራን ማህበር ሊቀ መንበር መምህር ከፍያለው አስፋው በበኩላቸው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲከናወን መምህራን የበኩላቸውን ሚና ይወጣሉ ብለዋል።

መምህራን በጠቅላላ ምርጫው በመራጭነት ከመሳተፍ በተጨማሪ የታዛቢነት ሚናቸውን እንዲወጡ ለማስቻል 11 የማህበሩ አባላት መለየታቸውን አስረድተዋል።

"7ኛው ጠቅላላ ምርጫ አካታችና አሳታፊ በሆነ መልኩ እንዲከናወን የበኩላችንን ሚና እየተወጣን ነው" ያሉት ደግሞ የብሔረሰብ አስተዳደሩ የአካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽን ሰብሳቢ አቶ ኪሮስ ቸኮለ ናቸው።

የፌዴሬሽኑ አባላትም የመምረጥ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ተጠቅመው ለአካል ጉዳተኞች ቅድሚያ ሰጥቶ የሚሰራ የፖለቲካ ፓርቲን ለመምረጥ የሚያስችላቸውን ካርድ ማውጣታቸውን አስረድተዋል።

በጠቅላላ ምርጫውም የፌዴሬሽኑ 50 አባላት በገለልተኝነት የታዛቢነት ሚና እንዲወጡ መለየታቸውንም አቶ ኪሮስ ገልፀዋል።

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ቦርዱ ባወጣው መርሃ ግብር መሰረት በመጪው ግንቦት 24/2018 ዓ/ም እንደሚካሄድ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም