ለሀገራዊ የሰርኩላር ኢኮኖሚ ፍኖተ ካርታ ትግበራ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት መጠናከር አለበት - ኢዜአ አማርኛ
ለሀገራዊ የሰርኩላር ኢኮኖሚ ፍኖተ ካርታ ትግበራ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት መጠናከር አለበት
አዲስ አበባ፤መጋቢት 9/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያን የሰርኩላር ኢኮኖሚ ፍኖተ ካርታ ስኬታማ ለማድረግ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎና ቅንጅት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሌሊሴ ነሜ (ዶ/ር) ገለጹ።
ባለስልጣኑ የፍኖተ ካርታውን ትግበራ ውጤታማ ለማድረግ ከተለያዩ የፌዴራል ተቋማት ጋር በጋራ መስራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሌሊሴ ነሜ(ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ባለስልጣኑ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን ውጤታማ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡
በዚህም ፅዱ ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ለውጥ የሚያመጡ የህግና አሰራር ስርዓት ወደ ተግባር በማስገባት ለሌሎች ሀገሮች ምሳሌ የሚሆኑ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልፀዋል።
የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ልማት ግቦችን ለማሳካትና ወደ ሰርኩላር ኢኮኖሚ የሚደረገውን ሽግግር ማፋጠን የሚያስችለው ሀገራዊ ፍኖተ ካርታ በ2017 ዓ.ም ተዘጋጅቶ ወደ ትግበራ መገባቱን አስታውሰዋል።
ፍኖተ ካርታው ፅዱ ኢትዮጵያን በመፍጠር ሂደት ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ የማዋል(Recycling) ባህልን የሚያበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን በማጎልበት፣ ለተሻለ ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታን በመፍጠርና አዳዲስ የስራ እድሎችን በመክፈት የሀገርን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ጉልህ ሚና ይጫወታል ብለዋል።
የአካባቢ ጥበቃ ስራ በአንድ ተቋም ብቻ ውጤታማ ማድረግ ስለማይቻል የባለድርሻ አካላትን ቅንጅት እንደሚጠይቅ ጠቅሰዋል።
በዚህም ወደ ሰርኩላር ኢኮኖሚ የሚደረገው ሽግግር እንዲፋጠን ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቁርጠኝነትና በተጠናከረ ተሳትፎ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ከተቋማቱ ጋር የተደረገው ስምምነት በአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ላይ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራትን ማከናወን፣ የህግና አሰራር ማሻሻያዎች፣ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ስርዓትን በቴክኖሎጂና በዕውቀት መደገፍ እንዲሁም የጋራ የድጋፍና ክትትል ስራዎችን በቅንጅት መስራት ከሚከናወኑ ሥራዎች መካከል ናቸው ብለዋል፡፡
ስምምነቱን ከተፈራረሙ ተቋማት መካከል የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ፈንታ ደጀን እንደገለጹት በባለስልጣኑ የተዘጋጀው ፍኖተ ካርታ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን ውጤታማ ለማድረግ ትልቅ ፋይዳ አለው፡፡
በሀገሪቱ የሚከናወኑ ግንባታዎች በመልሶ መጠቀም የተዘጋጁ የሀገር ውስጥ ግብዓቶችን እንዲጠቀሙ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ሃሰን መሃመድ በበኩላቸው የተዘጋጀው ፍኖተ ካርታ ከኢንዱስትሪ ዘርፉ ፖሊሲ ጋር የሚቀናጅ በመሆኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።
የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አለበል ደሴ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ የፖሊሲ ፋይዳ ያላቸው ሀገራዊ ጥናቶችን በመለየት ፖሊሲ አውጪውን የማማከር ስራ የሚሰራ ተቋም እንደመሆኑ ለፍኖተ ካርታው ትግበራ በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት የዋና ዳይሬክተር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሳባ ዘሪሁን በበኩላቸው በዚህ ስራ ባለድርሻ እንደመሆናችን የበኩላችንን አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁ ነን ብለዋል።