ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የኃይል ፍላጎትን በዘላቂነት ለማሟላት በትኩረት እየሰራች ነው-ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤መጋቢት 9/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የኃይል ፍላጎትን በዘላቂነት ለማሟላት በትኩረት እየሰራች መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ገለጹ።

ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የተፈጥሮ ኃብት በመጠቀም በካይ ያልሆኑ የኃይል ምንጮችን ለማልማት የረጅም ጊዜ ስትራቴጂ ነድፋ እየሰራች የምትገኝ ሲሆን የውሃ ኃይል፣ የንፋስና ፀሐይ ኃይል እንዲሁም የጂኦተርማል ተጠቃሾች ናቸው፡፡

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት ከምትጠቀመው አጠቃላይ የኃይል ምንጭ ውስጥ ከ96 በመቶ በላይ የሚሆነው በካይ ካልሆኑና ታዳሽ ከሆኑ ምንጮች የሚገኝ ነው።

ይህም ኢትዮጵያን በአረንጓዴ ኢነርጂ ልማት ረገድ ቀዳሚ ተጠቃሽ ሀገር እንድትሆን ያደርጋታል ብለዋል።

የውሃ ኃይል (Hydro) ትልቁን የኃይል ድርሻ የሚይዝ መሆኑን ጠቅሰው፥ የፀሐይና የንፋስ ኃይል ቴክኖሎጂዎችም በስፋት ወደ ስራ እየገቡ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ይህ ስኬት መንግስት ሀብቱን ወደዚህ ዘርፍ ለማዞር ባሳለፈው ፖሊሲ ተኮር ውሳኔ የተገኘ መሆኑን ጠቁመው፥ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የዚህ ስትራቴጂካዊ ውሳኔ ትልቁ አካል መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

መንግስት የዜጎችን የኃይል ፍላጎት ለማሟላት በአረንጓዴ ኢነርጂ ልማት ረገድ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የታላቁ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ ከሁሉም የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች የሚገኘው አጠቃላይ የኃይል መጠን ከ10 ጊጋ ዋት በላይ መድረሱ ከፍተኛ ሀገራዊ አቅም መፈጠሩን ያሳያል ብለዋል።

የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ጫና ለመቀነስና የአካባቢ ጥበቃን ለማረጋገጥ ከነዳጅ ነፃ የሆኑ አማራጮችን ማስፋፋት አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን አሳስበው በየደረጃው የታቀዱ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም