ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ኮሪደርና የአረንጓዴ ልማት ስኬቶች ለአፍሪካ ሀገራት ከተሞች ዕድገት ትምህርት የሚሰጥ ነው

አዲስ አበባ፤መጋቢት 9/2018 (ኢዜአ)፦የአዲስ አበባ ኮሪደርና የአረንጓዴ ልማት ስኬቶች ለአፍሪካ ሀገራት ከተሞች ዕድገት ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን የዛምቢያና ኢስዋቲኒ የአካባቢ ጥበቃ ሙያተኞች ገለጹ።

በአዲስ አበባ የተገነቡ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራ መዲናዋን ውብ ገፅታ በማላበስ ለነዋሪዎችና ጎብኝዎች ምቹ የእንቅስቃሴ ምኅደር ፈጥረዋል።

በመዲናዋ በአጭር ጊዜ የተመዘገቡ የልማት ውጤቶችም አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ዕውቅናን በማስገኘት ልምድና ተሞክሮ እየተቀሰመባቸው ይገኛል።

በአዲስ አበባ የተጀመረው የኮሪደር ልማትም ከተማዋን ውብ ገፅታ በማላበስ ነዋሪዎችን ምቹና የአረንጓዴ ከባቢ በማጎናጸፍ በ75 የኢትዮጵያ ከተሞች እየተተገበረ ይገኛል።

የዛምቢያና የኢስዋቲኒ የአካባቢ ጥበቃ ሙያተኞች ለኢዜአ እንዳሉት፤ አዲስ አበባ ከተማ የአፍሪካዊያን ማዕከልነቷን በተግባር ያረጋገጡ የልማት ውጤቶች ተገኝተዋል።

በመዲናዋ በአጭር ጊዜ የተገነቡ አስደናቂ የልማት ውጤቶችም ከተማዋን ውብ ገፅታ በማላበስ ምቹ የከተሜነት ምኅዳር እንዲፈጠር ማድረጉን ገልጸዋል።


 

በዛምቢያ የአካባቢና የገጠር ልማት ሚኒስቴር የደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ባለሙያ ብሬን ሲያካበያ፤ አዲስ አበባ ከጥቂት ዓመታት በፊት የተጎሳቆለና እርጅና የተጫጫነው ገፅታ እንደነበራት አስታውሰዋል።

በአሁኑ ወቅት በአጭር ጊዜ ውስጥ በአዲስ አበባ የተገነባው የኮሪደር ልማት ነዋሪዎች ምቹና ፅዱ የአረንጓዴ ከባቢን ያጎናጸፈ አስደናቂ ለውጥ መምጣቱን ገልጸዋል።

የመዲናዋ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችና ሰማይ ጠቀስ ህንፃዎች ተጠናቀው ለአገልግሎት መብቃታቸውም ውብ የከተሜነት ገፅታን በመፍጠር ልዩ ድምቀት እንደፈጠሩ ተናግረዋል።

በህዝብና በአመራር ቁርጠኝነት ተገንብተው የተጠናቀቁት የአዲስ አበባ የልማት ስኬቶችም ሀገራቸውን ጨምሮ ለአፍሪካ ሀገራት ከተሞች ዕድገት ትልቅ ትምህርት መሆኑን አንስተዋል።


 

የኢስዋቲኒ የአካባቢ ጥበቃ ዘርፍ የኢኮኖሚ ባለሙያ መሎሰም ቡሊ በበኩላቸው፣ ከተሜነት የአንድ ሀገር የዕድገትና ስልጣኔ መገለጫ ነው ብለዋል።

በአዲስ አበባ በአጭር ጊዜ የተገኙ ተምሳሌታዊ የኮሪደርና የአረንጓዴ ልማት ስኬቶች ዜጎች ዘመናዊ የከተሜነት አኗኗር ሥርዓት እንዲጎናጸፉ ያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የመዲናዋ አስደናቂ የከተማ ውበት፣የአረንጓዴና ቆሻሻ አያያዝ የልማት ስኬቶች የአፍሪካን የአየር ንብረት ለውጥና የአካባቢ መራቆት የመቀነስ ግብ ያገናዘቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማትም የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን በመቀነስ አህጉራዊ አጀንዳዎችን የሚያሳካና ትምህርት የሚቀሰምበት መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም