ቀጥታ፡

 በምርጫው የነቃ ተሳትፎ ለማድረግ ከወዲሁ የምርጫ ካርድ ወስደናል- የሐረር ከተማ  ነዋሪዎች 

ሐረር፤ መጋቢት 9/2018 (ኢዜአ)∶−በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በንቃት ለመሳተፍ የሚያስችላቸውን ካርድ ከወዲሁ መውሰዳቸውን  የሐረር ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚያካሄድ ይታወቃል። 

በከተማዋ በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች በመዘዋወር ኢዜአ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እንዳሉት በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ለመሳተፍ የምርጫ ካርዳችንን ወስደናል ሲሉ ተናግረዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡት የከተማው ነዋሪዎች መካከል የምርጫ ካርድ ስወስድ የመጀመርያዬ ነው ያለችው ወጣት አለምፀሃይ አበራ አንዷ ናት፤ የዜግነት መብቴን በመጠቀም የምርጫ ካርድ በመውሰዴ ደስተኛ ነኝ ብላለች።

በጠቅላላ ምርጫውም ለሰላም፣ ለልማትና ለዕድገት የሚሰራ ፓርቲ እንደምትመርጥ የተናገረችው ወጣት አለምጸሃይ  ወጣቶችም በምጫው የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉና ከወዲሁም የምርጫ ካርድ እንዲወስዱ የበኩሏን እየተወጣች ነው።

አቶ ደምመላሽ ለማ እንዳሉት በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ በጉጉት ስጠብቀው ነበር በዚህም “በምርጫዬ” አማካይነት የምርጫ ካርድ ተመዝግቤ ወስጃለሁ።

ምርጫ የዲሞክራሲ መብት መገለጫ ነው፤ ለአገርና ለህዝብ  ይጠቅማል ይበጃል የምንለውን የምንመርጥበት ነው ብለዋል።

ይህንን መብት ሁሉም የምርጫ ካርድ በመውሰድ መጠቀም እንደሚገባና ዕድሜው ለመራጭነት የደረሰ ሁሉ ምርጫ ካርድ በመውሰድ በንቃት መሳተፍ እንዳለበት አስተያየት ሰጥተዋል።

ምርጫ ለሰላም፣ ለልማትና ለዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አስፈላጊ በመሆኑ የምርጫ ካርድ መውሰዳቸውን የተናገሩት ደግሞ አቶ ኬይሩ ከሊል ናቸው።

በዚህም ኢትዮጵያን በልማት ሊያሳድግና ወደ ተሻለ የእድገት ደረጃ የሚያደርስ ፓርቲ ለመምረጥ  መዘጋጀታቸውን የጠቆሙት አቶ ኬይሩ እድሜው ለምርጫ የደረሰ ዜጋ ከወዲሁ የምርጫ ካርድ እንዲወስድ መክረዋል።

አቶ አደም ሙመድ በበኩላቸው ለአገርና ለህዝብ  ይጠቅማል፣ ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ደረጃ ያሻግራል የሚሉትን ፓርቲ  ለመምረጥ የምርጫ ካርድ በመውሰዳቸውን መደሰታቸውን  ተናግረዋል።

ምርጫ ለሰላምና ለዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው ዕድሜው ለመራጭነት የደረሰ ሁሉ ምርጫ ካርድ በመውሰድ በንቃት መሳተፍ አለበት ሲሉም አመልክተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም