ቀጥታ፡

በአሪ ዞን ማኅበረሰቡን ያሳተፈ የጎርፍ እና የናዳ ቅድመ መከላከል ሥራ እየተከናወነ ነው

ጂንካ፤ መጋቢት 9/2018 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አሪ ዞን ለጎርፍ እና ለናዳ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ማኅበረሰቡን በማሳተፍ አደጋን ቅድመ የመከላከል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የዞኑ አደጋ ሥጋትና ሥራ አመራር ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

የዞኑ አደጋ ሥጋትና ሥራ አመራር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አስራት አበበ እንደገለጹት፤ በአሪ ዞን የሚገኙ አራት ወረዳዎች በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጣቸው ተራራማና ተዳፋት በመሆናቸው በተደጋጋሚ ለናዳ አደጋ ተጋላጭ ናቸው። 

በተመሳሳይ በዞኑ የሚገኙ ሦስት ከተሞች ደግሞ ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ባለፈው ዓመት ወቅት በዎባ አሪ ወረዳ በተከሰተ የአፈር መንሸራተት በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ያስታወሱት ኃላፊው፤ በዘንድሮው ዓመትም በደቡብ አሪ ወረዳ ወሰት ቀበሌ መሰል አደጋ መከሰቱን ተናግረዋል። 

ዘንድሮ የተከሰቱት አደጋዎች ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸሩ በእጅጉ የቀነሱት ማኅበረሰቡን በማሳተፍ በተከናወኑ የመከላከል ሥራዎች መሆኑን አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅትም የበልግ ዝናብን ተከትሎ ሊከሰት የሚችለውን አደጋ ለመቀነስ  ለናዳ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ አርሶ አደሮችን ለጊዜው ከአካባቢው የማውጣት ሥራ እየተሰራ ነው።

በከተሞች በቆሻሻ የተደፈኑ የፍሳሽ ቦዮችን የማጽዳት ተግባር፤ ያልተጠበቀ የወንዝ ሙላት ለሰውና ለእንስሳት ሕይወት መጥፋት ምክንያት እንዳይሆን ማኅበረሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እየሰሩ ነው ብለዋል።

የደቡብ አሪ ወረዳ የወሰት ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ኃይሉ ከማይ በሰጡት አስተያየት፤ አካባቢያቸው ለናዳ ተጋላጭ መሆኑን በመገንዘብ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል። 

አደጋ እንዳይደርስባቸውም ለጊዜው ከአካባቢው በመራቅ ራሳቸውን እየጠበቁ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ሌላኛው የአስተያየት ሰጪ የባካ ዳውላ አሪ ወረዳ የሴኔጋል ቀበሌ ነዋሪ አቶ ማርቆስ አዲሱ በበኩላቸው፤ በአካባቢው በተከናወነው የተፋሰስ ልማት ሥራ ቀደም ሲል ይከሰት የነበረውን ናዳ መከላከል መቻላቸውን ገልጸዋል። 

ለናዳ ተጋላጭ በሆኑ ስፍራዎች ችግኞችን በመትከል አፈሩ እንዳይሸረሸር ጥበቃ እያደረግን ነው ያሉት አቶ ማርቆስ፤ በዚህም አደጋዎችን አስቀድሞ መከላከል መቻሉን አረጋግጠዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም