ቀጥታ፡

ጣልያን የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታን ለመደገፍ ፍላጎት እንዳላት ገለጸች

አዲስ አበባ፤መጋቢት 9/2018 (ኢዜአ)፦ጣልያን የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታን በገንዘብ ለመደገፍ ዝግጁ መሆኗን አስታወቀች።

በገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን፣ በሮም ከጣልያን የኢኮኖሚና ፋይናንስ ሚኒስትር ጂያንካርሎ ጂዮርጌቲ ጋር ውይይት አድርጓል።

ልዑካን ቡድኑ በጣልያን የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሚቱ ሀምቢሳ ጨምሮ የገንዘብ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን ያካተተ ነው።


 

በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ስትራቴጂካዊ የኢኮኖሚ ትብብርን ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር አድርጓል።

የጣልያን የኢኮኖሚና ፋይናንስ ሚኒስቴር ከዓለም ባንክ የበጀት ድጋፍ ፕሮግራም ጋር በተጓዳኝ የኢትዮጵያን የልማት ፖሊሲ ፕሮግራም በገንዘብ ለመደገፍ ተስማምቷል።

ይህ ድጋፍ ኢትዮጵያ አሁን ላይ እያከናወነች ላለው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ወሳኝ እገዛ እንደሚያደርግ የገንዘብ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መግለጫ አመልክቷል።

ጣልያን የኮይሻ የኤሌክሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትን ለማጠናቀቅ የቀረውን የገንዘብ ክፍተት ለመሙላት ጥረት እንደምታደርግ በመግለጽ ፕሮጀክቱን ለመደገፍ ያላትን ቁርጠኝነት ዳግም አረጋግጣለች።

ሁለቱም ወገኖች የብድር ማሻሻያና አዳዲስ የፋይናንስ ምንጮችን በመፈለግ ረገድ የታየውን ተጨባጭ ውጤት ያደነቁ ሲሆን፣ ቀሪ ጉዳዮችን በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።

በውይይቱ ላይ የሀገሪቱ ግዙፍ አገራዊ ፕሮጀክት በሆነው በቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ላይ በትብብር መሥራት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ምክክር ተደርጓል።


 

የጣልያን የኢኮኖሚና ፋይናንስ ሚኒስትር ጂያንካርሎ ጂዮርጌቲ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እያሳየ ያለውን ጠንካራ አፈጻጸም አድንቀው፤ ጣልያን በፋይናንስ ተቋሞቿ በኩል ለተመረጡ የፕሮጀክቱ ክፍሎች ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል።

ሁለቱም ወገኖች የፋይናንስ አወቃቀሮችንና ዝርዝር የአፈጻጸም ስልቶችን (modalities) ለመቅረጽ ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕን፣ የፋይናንስና የቴክኒክ አማካሪዎችን ያሳተፈ የቴክኒክ ውይይት እንዲጀመር ተስማምተዋል።

ለሌሎች ቅድሚያ ለሚሰጣቸው የልማት ፕሮጀክቶች ተጨማሪ ድጋፎችን ማሰባሰብ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይም መክረዋል።

በውይይቱ ላይ ሁለቱ ወገኖች ኢትዮጵያ እና ጣልያን ያላቸውን ወዳጅነት ይበልጥ ለማጠናከርና የጋራ ብልጽግናን የሚያረጋግጡ ስትራቴጂካዊ ስራዎችን ለማሳለጥ ቁርጠኛ እንደሆኑ መግለጻቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም