ወጣቶች በምርጫው ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው-የአፋር ክልል ወጣቶች ፌደሬሽን - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቶች በምርጫው ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው-የአፋር ክልል ወጣቶች ፌደሬሽን
ሰመራ፤ መጋቢት 9/2018(ኢዜአ)፡- ወጣቶች በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን የክልሉ ወጣቶች ፌዴሬሽን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው ሰሌዳ መሠረት ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ በመጪው ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ለማካሄድ የመራጮች ምዝገባና ሌሎች የቅድመ ምርጫ ተግባራትን እያከናወነ ነው፡፡
ምርጫውን በማስመልከት ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረው የአፋር ክልል ወጣቶች ፌዴሬሽን ኘሬዚዳንት ወጣት አፍክኤ አሊ ፌደሬሽኑ ከኢትዮጵያ ምርጫ ብሔራዊ ቦርድ በተሰጠው ሃላፊነት መሰረት የድርሻውን ለመወጣት እየሰራ ነው።
በዚህም ወጣቶች በምርጫ በንቃት እንዲሳተፉ ከማድረግ ባለፈ ህብረተሰቡን ስለምርጫ በማስገንዘብና በመቀስቀስ የበኩላቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ተናግሯል።
በቀጣይ ግንቦት ወር በሚካሄድ ጠቅላላ ምርጫ ወጣቶችን ከማስገንዘብ ባለፈ በታዛቢነት እንዲሳተፉ ወጣቶችን የመለየት ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል።
በዚህም ወጣቶች በክልሉ የተለያዩ ወረዳዎች ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ነጻ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከታዛቢነት ሚናቸው ባለፈ ድምጽ በመስጠት በንቃት እንደሚሳተፉ አመልክተዋል።
የዱብቲ ከተማ ነዋሪ ወጣት አህመድ ያዮ በበኩሉ እንደተናገረው በዘንድሮ ምርጫ ሀገርና ህዝብን በተሻለ ሊመራ ይችላል፣ ወጣቶችንም ተጠቃሚ ያደርጋል የሚለውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅቷል።
ሀገርን መምራት የሚችለው በምርጫ ያሸነፈ ፓርቲ መሆኑን በመረዳት የምፈልገውን ፓርቲ መምረጥ የሚያስችለኝን የምርጫ ካርድ አስቀድሜ ወስጃለሁ ሲለም ግልጿል፡፡
ህብረተሰቡም በተለይ ወጣቱ ከወዲሁ የመራጭነት ካርድ በመውስድ ዴሞክራሲያዊ መብቱን እንዲጠቀም አስገንዝቧል።
የሰመራ ከተማ ነዋሪ ወጣት ሐዋ ኢድሪስ በበኩሏ በዘንድሮው ምርጫ በንቃት ለመሳተፍ ካርድ ወስዳ የምርጫ ቀኑን እየተጠባበቀች መሆኗን ተናግራለች።
ሌሎች የአካባቢዋ ሴቶችም የሴቶችን ጥያቄ ለመመለስ በቁርጠኝነት የሚሰራ የፖለቲካ ፓርቲን በመምረጥ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን በተግባር እንዲያረጋግጡ የማስገንዘብ ሥራ መጀመሯን ነው የገለጸችው።
በቀጣይ ሀገርን ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የሚያስቀጥልና በልማት የሚያሻግር ፓርቲ ለመምረጥ ዛሬ ካርድ መውሰድ ስለሚያስፈልግ ሁሉም መዘናጋት እንደሌለበት መክራለች።