ኢትዮጵያ እና ጣልያን የእዳ ሽግሽግ ስምምነት ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና ጣልያን የእዳ ሽግሽግ ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ፤መጋቢት 9/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ እና ጣልያን ስትራቴጂካዊ አጋርነታቸውን የሚያጠናክር የእዳ ሽግሽግ ስምምነት ተፈራርመዋል።
ስምምነቱን የተፈራረሙት የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ እና የጣልያን የኢኮኖሚና ፋይናንስ ሚኒስትር ጂያንካርሎ ጂኦርጌቲ ናቸው።
የእዳ ሽግሽግ ስምምነቱ የቡድን 20 (G20) የጋራ ማዕቀፍ ስር ያለው የኦፊሴላዊ አበዳሪዎች ኮሚቴ (OCC) ሂደት አካል ነው።
የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ጣልያን ላሳየችው ገንቢ ተሳትፎ እና አመራር ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የጣልያን ቁርጠኝነት እ.ኤ.አ. በሐምሌ 2025 የመግባቢያ ስምምነት ላይ ለመድረስ እና የሁለትዮሽ ስምምነቱን በስኬት ለማጠናቀቅ ቁልፍ ሚና መጫወቱን አመልክተዋል።
የጣልያን የኢኮኖሚና ፋይናንስ ሚኒስትር ጂያንካርሎ ጂኦርጌቲ በበኩላቸው፥ ስምምነቱ ኢትዮጵያ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ቅድሚያ ከምትሰጣቸው ጉዳዮች ጋር የተጣጣመ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ስምምነቱ ኢትዮጵያ ቁልፍ አጋር ሀገር በሆነችበት የጣልያን “የማቴይ እቅድ ለአፍሪካ” (Mattei Plan for Africa) ስኬት የራሱን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት መናገራቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መረጃ አመልክቷል።
በገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ የተመራ ልዑክ የኢትዮጵያ እና ጣልያን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር ያለመ ጉብኝት በጣልያን ሮም እያደረገ ይገኛል።
የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ እ.አ.አ 2022 ይፋ ያደረጉት የማቴይ እቅድ ጣልያን ከአፍሪካ ጋር ያላት የኢኮኖሚ እና የልማት ትብብር ማጠናከርን ያለመ ነው።
የ5 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዩሮ የስትራቴጂክ ማዕቀፉ በጣልያኑ የብሄራዊ የዘይት እና ነዳጅ ኩባንያ መስራች ኤነሪኮ ማቴይ የተሰየመ ነው።
ኩባንያው ከአፍሪካ ጋር ከአጭር ጊዜ እርዳታ የረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ ትብብርን በማስቀደም እየሰራ እንደሚገኝ ተመላክቷል።
የአፍሪካን የኢኮኖሚ እድገት መደገፍ፣ የስራ እድሎችን ማስፋት፣ አፍሪካን የአውሮፓ የኢነርጂ አቅራቢ አጋር የማድረግ ስራን ማስተዋወቅ፣ለአፍሪካውያን የኢኮኖሚ ችግሮች መፍትሄ በመስጠት ኢ-መደበኛ ፍልሰትን ከምንጩ ማድረቅ እንዲሁም ከበጎ አድራጎት የተላቀቀ የጋራ ተጠቃሚነት እና ትብብርን መፍጠር የእቅዱ አበይት አላማዎች ናቸው።