የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ አፍሪካን በልኳ ለዓለም የሚያስረዳ ትርክት መገንባት ያስችላል - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ አፍሪካን በልኳ ለዓለም የሚያስረዳ ትርክት መገንባት ያስችላል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 8/2018 (ኢዜአ)፦ የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ አፍሪካን በልኳ ለዓለም የሚያስረዳ ትርክት መገንባት የሚያስችል መሆኑን የፐልስ ኦፍ አፍሪካ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍጹምእሸት ሽመልስ ገለጹ፡፡
ኢትዮጵያ በራሷ አቅም ያስመዘገበቻቸው ለአፍሪካ ኩራት የሆኑ ዓለም የመሰከረላቸው ድሎችን ለማስተዋወቅ ያግዛልም ብለዋል፡፡
የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ በመጭው ሚያዚያ 29 እና 30 ቀን 2018 ዓ.ም በዓድዋ ድል መታሰቢያ ይካሄዳል።
ፐልስ ኦፍ አፍሪካ /pulse of Africa/ ከኤ.ጂ.ኤ የቴክኖሎጂ ኢንተርፕራይዝ ጋር በመተባበር የሚያዘጋጀው ጉባዔ "ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ለተሻለች አፍሪካ" የሚል መሪ ሀሳብ ይዟል።
የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ጉባዔ ሀላፊነት የሚሰማቸው የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎችን ለማበረታታት፣ ዲጂታል ኢኮኖሚን ለማጠናከር፣ ትብብርን ለመፍጠርና አዲስ አበባን የባህልና የዲጂታል ማዕከል ለማድረግ ያለመ ነው።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት፣ በመንግሥታቱ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽንና የሌሎች አሕጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት መገኛ የዓለም የዲፕሎማሲ ማዕከል፣ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የነደፈች፣ አህጉራዊ የመተላለፊያ በር በመሆኗ አዲስ አበባ ለማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ጉባዔ ተመራጭ ያደርጋታል።
በዚህም በቀጣይ ሚያዚያ 2018 ዓ.ም መጨረሻ በሚካሄደው የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ጉባዔ ኢትዮጵያውያን የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች በንቃት መሳተፍ በሚችሉባቸው ዕድሎች ዙሪያ ውይይት ተደርጓል።
የፐልስ ኦፍ አፍሪካ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍጹምእሸት ሽመልስ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የአፍሪካን ገንቢ ትርክት ለመገንባት በአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች እጅ ነው።
አፍሪካ የትርክት ተጎጂ መሆኗን ገልጸው፤ ፐልስ ኦፍ አፍሪካ የአፍሪካ ትርክትን ለመቀየር የተቋቋመ አፍሪካዊ ሚዲያ መሆኑን ተናግረዋል።
ፐልስ ኦፍ አፍሪካ መነሻው ኢትዮጵያ መዳረሻው አፍሪካ ነው ያሉት ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ ከማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ጋር በመተባበር የአፍሪካን ትክክለኛ ገፅታ ለዓለም እንደሚያስተዋውቅ ገልጸዋል።
አፍሪካ የራሷን በጎ ትርክት ለመገንባት በምታደርገው ጥረት ፐልስ ኦፍ አፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎችን በማስተባበር መሪ ተዋናይ ሆኖ ይሰራል ብለዋል፡፡
የማህበራዊ ሚዲያዎች አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተፅዕኖዎች የጎላ ነው ያሉት ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ በጉባዔው ላይ ኢትዮጵያውያን ተፅዕኖ ፈጣሪዎች የሀገራቸውን መልካም ገጽታ እንዲገነቡና ትብብር እንዲፈጥሩ ጠይቀዋል።
ኢትዮጵያ በራሷ አቅም ያስመዘገበቻቸው ለአፍሪካ ኩራት የሆኑ ዓለም የመሰከረላቸው ድሎችን ለማስተዋወቅ ገንቢ ሚና እንዳለውም ገልጸዋል፡፡
በቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪዝም ፕሮሞሽን መሪ ሥራ አስፈፃሚ ተሾመ ተክሉ፤ ኢትዮጵያ የቅርስ፣ የታሪክና የባህል ባለቤት መሆኗን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ያላትን ዕምቅና ዘርፈ ብዙ የቱሪዝም ሀብት አውጥቶ ማሳየት ሳይቻል መቆየቱን ያወሱት መሪ ሥራ አስፈፃሚው፤ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ለኢትዮጵያ ቱሪዝም ትልቅ ሀብቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።
የማህበራዊ ሚዲያን ለበጎ ዓላማ መጠቀም ከተቻለ ሀገራዊ የቱሪዝም ሀብትን ለዓለም ማሳየት የሚያስችል መድረክ ነውም ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች የሀገራቸውን የቱሪዝም ሀብት ሲያስተዋውቁ የቱሪዝም ሚኒስቴር አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡
የቱሪዝም ሚኒስቴር ለማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች በሩ ክፍት ነው ያሉት መሪ ሥራ አስፈፃሚው፤ የቱሪዝም ሀብቶችን ለማየት ለሚፈልጉ ሁሉ ምቹ ሁኔታ እንፈጥራለን ብለዋል።
የኤጂኤ ቴክ ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ገመዳ ኦላና፤ ጉባኤው የኢትዮጵያ ብሎም የአፍሪካን ገፅታ ለመገንባት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች የእርስ በእርስ ትብብራቸውን በማጠናከር አህጉራዊ አንድነትን መፍጠር ያስችላል ብለዋል።
በመድረኩ የተሳተፉ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች በበኩላቸው፤ ሁነቱ የኢትዮጵያን ገፅታ ለመገንባት ብሎም የአፍሪካን ትክክለኛ ትርክት ለመገንባት ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ በኢትዮጵያ መዘጋጀቱ የሀገራችንን ገጽታ ለመገንባት የቱሪዝም ሃብታችንን ለማስተዋወቅ ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
የጉባዔው አዘጋጆች ምስጋና ይገባቸዋል ያሉት ተሳታፊዎቹ፤ ለሁነቱ መሳካት በትብብር ለመስራትና የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል፡፡