በታላቁ የረመዳን ወር የሚከናወነው የኢፍጣር መርሃ ግብር አብሮነትና መተሳሰብን ይበልጥ የሚያጠናክር ነው-ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ - ኢዜአ አማርኛ
በታላቁ የረመዳን ወር የሚከናወነው የኢፍጣር መርሃ ግብር አብሮነትና መተሳሰብን ይበልጥ የሚያጠናክር ነው-ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ
ጋምቤላ፤መጋቢት 8/2018 (ኢዜአ)፦በታላቁ የረመዳን ወር የሚከናወነው የኢፍጣር መርሃ ግብር አብሮነትና መተሳሰብን ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑን የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ ገለጹ።
የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የእምነቱ አባቶችና ምዕመናን የታደሙበት የኢፍጣር መርሃ ግብር ዛሬ ምሽት በጋምቤላ ከተማ ተካሄዷል።
ርዕሰ መስተዳድሯ በመርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው እንዳሉት፥ በታላቁ የረመዳን ወር የሚከናወነው የኢፍጣር መርሃ ግብር አብሮነትና መተሳሰብን ይበልጥ የሚያጠናክር ነው።
በታላቁ የረመዳን ወር ሕዝበ ሙስሊሙ ማዕድ ከማጋራት ባለፈ የመተጋገዝና የመረዳዳት እሴቶችን በተሻለ መልኩ ሲከውን መቆየቱን ገልጸዋል።
የኢፍጣር መርኃ ግብሩ በህዝቦች መካከል ያለውን አንድነት፣ፍቅርና መተሳሰብን በማጎልበት ለትውልድ የምትተርፍ ጠንካራ ሀገርን ለመገንባት አቅም የሚሆን ነው ብለዋል።
በረመዳን ወቅት የታየው መተዛዘንና መተሳሰብ ከረመዳን ወር በኋላም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድሯ አስገንዝበዋል።
የጋምቤላ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ አህመድ የሱፍ በበኩላቸው፥ ታላቁ የረመዳን ወር የመተዛዘን፣የአንድነትና የመደጋገፍ ባህል ጎልቶ የሚታይበት ወር መሆኑን ተናግረዋል።
በእስልምና አስተምህሮዎች አብሮ መብላትና የተቸገሩትን መደገፍ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠው እሴት መሆኑንም ገልፀዋል።
የኢፍጣር መርሃ ግብሩ ለሰው ልጅ ክብር መስጠት፣ርህራሄን እና አብሮነት በተግባር የሚታይበት መሆኑንም ተናግረዋል።