ቀጥታ፡

አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን ጨምሮ ለደን ልማት በተሰጠው ትኩረት የደን ሽፋን ጨምሯል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 8/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን ጨምሮ ለደን ልማት የተሰጠው ትኩረት ሀገራዊ የደን ሽፋኑ እንዲያድግ ማስቻሉን የኢትዮጵያ የደን ልማት አስታወቀ።      

የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር ከበደ ይማም መጋቢት 12 ቀን 2018 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚከበረውን 14ኛው የዓለም የደን ቀንን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።    

ዋና ዳይሬክተሩ በመግለጫቸው፤ በኢትዮጵያ ከፍተኛ የደን ጭፍጨፋ እንደነበር አስታውሰው፤ በዚህም የኢትዮጵያ የደን ሽፋን በዕጅጉ ቀንሶ እንደነበር አስረድተዋል።  

ለአብነትም ከአስር ዓመት በፊት በየዓመቱ ዘጠና ሁለት ሺህ ሄክታር መሬት ደን ይጨፍጨፍ ነበር ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ አሁን ላይ ወደ ሃያ ሰባት ሺህ ሄክታር ዝቅ እንዲል መደረጉን ተናግረዋል።  

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን ጨምሮ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ለደን ልማት የተሰጠው ትኩረት በመስኩ ትልቅ ውጤት እንዲመጣ ማስቻሉን አብራርተዋል።  

ከሀገራዊ ለውጡ በፊት 17 ነጥብ 2 በመቶ የነበረው የደን ሽፋን አሁን ላይ ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ከፍ ማለቱን ተናግረዋል።   

14ኛው የዓለም የደን ቀንም በኢትዮጵያ በዘርፉ የተገኙ ስኬቶች ከማጉላት ባለፈ የባለድርሻ አካላትን ቅንጅት ይበልጥ በማጠናከር ለላቀ ውጤታማነት የሚመከርበት ነው ብለዋል።   

በኢትዮጵያ የደን ሽፋን እያደገ መምጣቱን ተከትሎ በርካታ ውጤቶች እየተገኘ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የውኃ አቅርቦት እንዲሻሻል፣ የተጎዱ መሬቶች እንዲያገግሙ ማስቻሉንም ገልጸዋል።

ይህም ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ከማገዝ ባለፈ ብዝሃ ህይወት እንዲጠበቁ አወንታዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ብለዋል። 

በተለይም ሙቀት አማቂ ጋዞችን በመቀነስ ረገድ የኢትዮጵያ የደን ኃብት ከፍ ያለ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ስጋት የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል በሚደረገው ጥረትም ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተችና ለዚህ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ተጠቃሽ ማሳያ ነው ብለዋል።   

14ኛው የዓለም የደን ቀን "ደን ለኢኮኖሚ" በሚል መሪ ሀሳብ ይከበራል።    

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም