በጋሞ ዞን በደረሰው አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የምግብና የዓይነት ድጋፍ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በጋሞ ዞን በደረሰው አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የምግብና የዓይነት ድጋፍ ተደረገ
አርባ ምንጭ፤ መጋቢት 8/2018 (ኢዜአ)፦ በጋሞ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የምግብና የዓይነት ድጋፍ ተደረገ።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም በአደጋው ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች 6 ሚሊዮን ብር የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።
የክልሉ ዩኒቨርስቲዎች ፎረም ያደረገውን ድጋፍ ጨምሮ በዛሬው እለት በተለያዩ አካላት በጠቅላላው ከ7 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያለው የምግብና የዓይነት ድጋፍ መደረጉም ታውቋል።
የዩኒቨርሲቲዎቹ ፎረም አባልና የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮሐንስ ይትባረክ እንዳሉት በድጋፉ ዘይት፣ ዱቄት፣ ማካሮኒ፣ ፍራሽ፣ አልባሳትና ሌሎች ለአስቸኳይ ጊዜ የሚሆኑ ቁሳቁስን መካተቱን ተናግረዋል።
ድጋፉ 6 ሚሊዮን የሚገመት ሲሆን በፎረሙ በታቀፉ ጂንካ፣ ዲላ፣ ወላይታ ሶዶ እና አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲዎች በጋራ የተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይም ጋሞ ዞንን ጨምሮ ሌሎች በክልሉ ለተፈጥሮ አደጋ ተጋላጭ ለሆኑ አካባቢዎች ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት የሚያስችሉ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ለማካሄድ የሚያስችል እንቅስቃሴ መጀመሩንም አስረድተዋል።
በተመሳሳይም የደቡብ ኦሞ ዞን፣ በአርባ ምንጭ ከተማ የሚገኙ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ተጠሪ ተቋማት እና በአዲስ አበባ የጋሞ አካባቢ ተወላጆችና ወዳጆች መረዳጃ ዕድር ግምታቸው ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል።
የደቡብ ኦሞ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የውሃና ኢነርጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ ታደለ ጋያ በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች በደረሰ አደጋ የዞኑ አስተዳደርና ህዝብ በእጅጉ ማዘናቸውን ተናግረዋል።
ዞኑ ዛሬ ያደርገው ድጋፍ ግምታቸው ግማሽ ሚሊዮን ብር የሆነ ዱቄት፣ ዘይት፣ ፍራሽ፣ የመጠለያ ሸራ እና ሌሎች ቁሳቁስ መሆናቸውን አመልክተዋል።
በአደጋው የተጎዱ ወኖች በዘላቂነት እስኪቋቋሙ ድረስ ድጋፉን አጠናክሮ ለማስቀጠል በደቡብ ኦሞ ዞን ባሉ የወረዳና የከተማ መዋቅሮች ሀብት የማሰባሰብ ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም አስታውቀዋል።
በአርባ ምንጭ ከተማ የሚገኙ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ተጠሪ ተቋማትም 300 ሺህ ብር የሚገመት የምግብና የዓይነት ድጋፍ አድርገዋል፡፡
የአርባ ምንጭ ትምህርት ኮሌጅ ዲን እንዳለ ኤርሚያስ (ዶ/ር) ድጋፉ የተደረጋው ኮሌጁን ጨምሮ የአርባምንጭ ፖሊ ቴክኒክ ኢንስቲትዩት እንዲሁም በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የአርባ ምንጭ ቅርንጫ ጽህፈት ቤት በጋራ በመሆን መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የጋሞ አካባቢ ተወላጆችና ወዳጆች መረዳጃ ዕድርም 320 ሺህ ብር በአደጋው ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች አድርጓል።
የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ደምሴ አድማሱ (ዶ/ር) በበኩላቸው አደጋው ከተከሰተ ጀምሮ የተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት፣ ተቋማትና ግለሰቦች ሀዘናቸውን በመግለፅ የተለያዩ ድጋፎችን ለተጎጂዎች እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
በዛሬው እለትም ለተጎጂዎች የተለያየ ድጋፍ ያደረጉ ተቋማትን አመስግነው በቀጣይ ተጎጂዎችን ለማቋቋምና በአካባቢው ላይ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት የዞኑ አስተዳደር ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ ከተለያዩ አካላት ጋር በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።