ቀጥታ፡

ከተማ አስተዳደሩ 315 የንግድ ሱቆችን ለኮሪደር ልማት ተነሺዎች በዕጣ አስተላለፈ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 8/2018 (ኢዜአ)፦የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዛሬ በኮሪደር ልማት የተገነቡ 315 የንግድ ሱቆችን፣ በቀበሌና በንግድ ቤቶች በኪራይ ሲሰሩ ለነበሩ የኮሪደር ልማት ተነሺዎች በዕጣ አስተላልፏል ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

አስተዳደሩ ከዚህ ቀደም የመንግስት የቀበሌና የንግድ ቤቶችን ተከራይተው ሲሰሩ ለነበሩ ነዋሪዎች አስተዳደራችን ሁለት አማራጮችን አቅርቦ እንደየምርጫቸው በአክሲዮን ተደራጅተው ወደ ንግድ ሱቃቸው ገብተው ሥራ እንዲጀምሩ፣ ይህ ካልሆነም መንግስት የሚያቀርብላቸውን ሱቆች ተከራይተው እንዲሰሩ እድል ሰጥቶ እንደነበር ከንቲባ አዳነች ገልጸዋል።


 

አብዛኛዎቹ መንግስት ገንብቶ ያቀረበላቸውን ሱቆች ተከራይተው ንግዳቸውን የቀጠሉ ሲሆን፣ በአክሲዮን ተደራጅተው ወደ ንግድ ሱቃቸው ገንብተው ለመነገድ የመረጡም በርካቶች ነበሩ ብለዋል።

ከእነዚህ በአክሲዮን እንዲደራጁና መሬት ተረክበው እንዲገነቡ ከተፈቀደላቸው ውስጥ የመገንባት አቅም በማጣታቸው በተለያዩ የውይይት መድረኮች ሌላ አማራጭ እንዲሰጣቸው ሲጠይቁ መቆየታቸውንም ጠቁመዋል።

በመሆኑም አስተዳደሩ ችግሩን ለመቅረፍ፤ በኮሪደር ልማት፣ በወንዝ ዳርቻ ልማት እና በመልሶ ማልማት ሥራዎች ምክንያት ለተነሱ ነዋሪዎች፤ በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች በኮሪደር ልማቱ የተገነቡ 315 ዘመናዊ የንግድ ሱቆችን በዕጣ እንዲተላለፉላቸው ማድረጉን ነው በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው የገለጹት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም