የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች የአፍሪካን ትርክት በጋራ ለመቅረፅ ገንቢ ሚና አላቸው - ኢዜአ አማርኛ
የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች የአፍሪካን ትርክት በጋራ ለመቅረፅ ገንቢ ሚና አላቸው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 8/2018 (ኢዜአ)፦ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች የአፍሪካን ትርክትና ህልም በጋራ ለመቅረፅ ገንቢ ሚና እንዳላቸው የፐልስ ኦፍ አፍሪካ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍጹምእሸት ሽመልስ ገለጹ።
የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ስብሰባ በመጭው ሚያዚያ 29 እና 30 ቀን 2018 ዓ.ም በዓድዋ ድል መታሰቢያ ይካሄዳል።
ፐልስ ኦፍ አፍሪካ /pulse of Africa/ ከኤ.ጂ.ኤ የቴክኖሎጂ ኢንተርፕራይዝ ጋር በመተባበር የሚያዘጋጀው ስብሰባ "ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ለተሻለች አፍሪካ" የሚል መሪ ሀሳብ ይዟል።
የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ስብሰባ ሀላፊነት የሚሰማቸው የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎችን ለማበረታታት፣ ዲጂታል ኢኮኖሚን ለማጠናከር፣ ትብብርን ለመፍጠርና አዲስ አበባን የባህልና የዲጂታል ማዕከል ለማድረግ ያለመ ነው።
የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች አፍሪካ የራሷን ትርክት መገንባት የሚያስችሉ፣ የደንበኞችን እምነት የሚያሳድጉ፣ ብራንድ ለመፍጠር ወሳኝ መሆናቸው ስብሰባውን አስፈላጊ ያደርገዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት፣ በመንግሥታቱ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽንና የሌሎች አሕጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት መገኛ የዓለም የዲፕሎማሲ ማዕከል፣ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የነደፈች፣ አህጉራዊ የመተላለፊያ በር በመሆኗ አዲስ አበባ ለማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ስብሰባ ተመራጭ ያደርጋታል።
በዚህም በቀጣይ ሚያዚያ 2018 ዓ.ም መጨረሻ በሚካሄደው የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ስብሰባ ኢትዮጵያውያን የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች በንቃት መሳተፍ በሚችሉባቸው ዕድሎች ዙሪያ ከዘርፉ ተዋንያን ጋር ውይይት ተደርጓል።
የፐልስ ኦፍ አፍሪካ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍጹምእሸት ሽመልስ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የአፍሪካን ገንቢ ትርክት ለመገንባት በአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች እጅ ነው።
አፍሪካ የትርክት ተጎጂ መሆኗን ገልጸው፤ ፐልስ ኦፍ አፍሪካ የአፍሪካ ትርክት ለመቀየር የተቋቋመ አፍሪካዊ ሚዲያ መሆኑን ተናግረዋል።
ፐልስ ኦፍ አፍሪካ መነሻው ኢትዮጵያ መዳረሻው አፍሪካ ነው ያሉት ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ ከማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ጋር በመተባበር የአፍሪካን ትክክለኛ ገፅታ ለዓለም እንደሚያስተዋውቅ ገልጸዋል።
ማህበራዊ ሚዲያዎች አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተፅዕኖዎቹ የጎላ መሆኑን አመልክተው፤ በስብሰባው ላይ ኢትዮጵያውያን ተፅዕኖ ፈጣሪዎች የሀገራቸውን መልካም ገጽታ እንዲገነቡና ትብብር እንዲፈጥሩ ተናግረዋል።
በቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪዝም ፕሮሞሽን መሪ ሥራ አስፈፃሚ ተሾመ ተክሉ፤ ኢትዮጵያ የቅርስ፣ የታሪክና የባህል ባለቤት መሆኗን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ያላትን ዕምቅና ዘርፈ ብዙ የቱሪዝም ሀብት አውጥቶ ማሳየት ሳይቻል መቆየቱን ያወሱት መሪ ስራ አስፈፃሚው፤ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ለኢትዮጵያ ቱሪዝም ትልቅ ሀብቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።
የማህበራዊ ሚዲያን ለበጎ ዓላማ መጠቀም ከተቻለ ሀገራዊ የቱሪዝም ሀብትን ለዓለም ማሳየት የሚቻልበት መድረክ ነውም ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች የሀገራቸውን የቱሪዝም ሀብት ሲያስተዋውቁ የቱሪዝም ሚኒስቴር አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
የቱሪዝም ሚኒስቴር ለማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች በሩ ክፍት ነው ያሉት መሪ ሥራ አስፈፃሚው፤ የቱሪዝም ሀብቶችን ለማየት ለሚፈልጉ ሁሉ ምቹ ሁኔታ እንፈጥራለን ብለዋል።
ኤጂኤ ቴክ ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ገመዳ ኦላና በበኩላቸው፤ ስብሰባው የኢትዮጵያ ብሎም የአፍሪካን ገፅታ ለመገንባት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች የእርስ በእርስ ትብብራቸውን በማጠናከር አህጉራዊ አንድነትን መፍጠር ያስችላል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ያላትን ከፍተኛ የተደማጭነት ሚና በማሳደግ የጎላ አበርክቶ እንደሚኖረው ገልጸዋል።