በክልሉ የግብርና ግብዓት ጥራትና አቅርቦትን በማሳደግ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት የማጎልበት ተግባራት ይጠናከራሉ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የግብርና ግብዓት ጥራትና አቅርቦትን በማሳደግ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት የማጎልበት ተግባራት ይጠናከራሉ
ቁሊቶ፤ መጋቢት 8/2018 (ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የግብርና ግብዓት ጥራትና አቅርቦትን በማሳደግ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት የማጎልበት ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የክልሉ የግብርና ግብአት ህገ-ወጥ ዝውውር ቁጥጥር ግብረ ሃይልና ባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ በሀላባ ቁሊቶ ከተማ ተካሄዷል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ዑስማን ስሩር በመድረኩ እንዳሉት መንግሥት ግብርናውን በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።
በክልሉ ጥራት ያለውን የግብርና ግብዓት ለአርሶ አደሩ ተደራሽ በማድረግ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተከናወነ ያለው ተግባር ውጤት እንዳመጣ ገልጸዋል።
በመሆኑም በክልሉ የግብርና ግብዓት ጥራትና አቅርቦትን በማሳደግ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት የማጎልበት ተግባራት ይጠናከራሉ ብለዋል።
ከግብዓት አቅርቦት ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ውስንነቶችንና ህገ ወጥነትን ለመከላከል የሚያስችል ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ተግባር መግባቱንም አቶ ኡስማን ጠቁመዋል።
ግብረ ሀይሉ የግብርና ግብዓት ጥራት፣ ቁጥጥርና ክትትል በማድረግ ምርታማነትን በማሳደግ ለአርሶ አደሩ ተጠቃሚነት መረጋገጥ እያከናወነው ያለው ተግባር ውጤታማ ነው ብለዋል።
ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚረዱ የምርጥ ዘር፣ የአፈር ማዳበሪያ፣ የጸረ ተባይና የአነስተኛና የእርሻ መሳሪያ አቅርቦት ጥራት ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው ያሉት ደግሞ የክልሉ የግብርና ግብዓቶች ጥራት ቁጥጥርና ኳሪንቲን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አብዱልሀኪም አልቤ (ዶ/ር) ናቸው።
የግብርና ግብዓትን በህገ ወጥ መንገድ በሚያቀርቡ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝ ጠቁመው በግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተያዘውን ግብ ለማሳካት ቁጥጥሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡
የደቡብ ምርጥ ዘር ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ በላይ ሀሪሶ ለበልግና መኸር ወቅት የሚሆን ከ115 ሺህ በላይ ኩንታል ምርጥ ዘር ለአራቱም ክልሎች እየቀረበ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
ድርጅቱ የስንዴና የበቆሎን ጨምሮ የተለያዩ የቅባት እህሎችን የዘር ብዜት በማከናወን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ የገለፁት ደግሞ የዘርፉ አዝርዕት ልማት ድርጅት ስራ አስኪያጅ አቶ አብርሃም ትንሳኤ ናቸዉ፡፡
የሚያቀርቡት ምርጥ ዘር ጥራት ያለው እንዲሆን ከግብረ ሀይሉ ጋር ተቀራርበው እየሰሩ እንደሚገኙ ጠቁመው ተገቢ ያልሆነ የምርጥ ዘር አቅራቢዎችን በመከላከል ረገድ የግብረ ኃይሉ አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተመሳሳይም በእንስሳት ጤና አጠባበቅ ዙሪያ ለባለድርሻ አካላት የተዘጋጀ ስልጠና በቁሊቶ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
በመርሃ ግብሩ ላይም በክልሉ ባለፉት ዓመታት የእንስሳት እርባታ ዘርፉን ከሌማት ትሩፋት ኢንሼቲቭ ጋር በማስተሳሰር በተከናወነው ተግባር ተጨባጭ ውጤት እንደተመዘገበም ተመልክቷል።
በዓሳ፣ በዶሮና በንብ ማነብ ስራም ምርታማነትን ከማሳደግ በተጨማሪ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር መቻሉም ተገልጿል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የዞን የግብርና መምሪያ ኃላፊዎችና ባለ ድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡