ቀጥታ፡

የኃይማኖት ተቋማት ትውልድን በሥነ-ምግባር የመቅረፅ ገንቢ ሚናቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል-ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤መጋቢት 8/2018(ኢዜአ)፦የኃይማኖት ተቋማት ትውልድን በሥነ-ምግባር የመቅረፅ ገንቢ ሚናቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ''የኃይማኖት ተቋማት በመደመር መንግስት ዕይታ” በሚል መሪ ሃሳብ ከኢትዮጵያ ወንጌላውያን፣ ከካቶሊክ እና ከሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተክርስቲያናት ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል።


 

"የኃይማኖት ተቋማት በመደመር መንግሥት እይታ" በሚል የውይይት መነሻ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ የመደመር መንግሥት የኃይማኖት ተቋማት በሀገረ መንግስት ግንባታ ዋልታና ማገር ሆነው ለማገልገላቸው ዕውቅና እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ትውልድን በሥነ-ምግባር በመቅረጽ ረገድም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውንና በተለያዩ ተልዕኮዎች በልማት ስራዎች ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ከተማ አስተዳደሩ የኃይማኖት ተቋማት የሚያቀርቡትን ጥያቄ በፍትሐዊነት ምላሽ እየሰጠ እንደሚገኝ አንስተዋል።

በኃይማኖት ሽፋን የሚደረጉ ያልተገቡ አካሄዶችን በሕግ አግባብ ሥርዓት ማስያዝም ከሁሉም የሚጠበቅ ተግባር መሆኑን አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ የሁሉንም የተደመረ አቅም ትፈልጋለች ያሉት ከንቲባዋ፤የኃይማኖት ተቋማት ትውልድን በሥነ-ምግባር በመቅረጽ ሂደት ውስጥ ገንቢ ሚናቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አመላክተዋል።

የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር ዓባይ፤ ከተማ አስተዳደሩ የኃይማኖት ተቋማት ለሚያቀርቧቸው ጥያቄዎች ምላሽ እየተሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የኃይማኖት ተቋማት በከተማዋ ልማትና ሰላም ግንባታ ላይ እያበረከቱ ያለውን ጉልህ አስተዋጽኦ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ገልጸዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፤በአዲስ አበባ ከተማ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ዘርፈ ብዙ የልማት ስኬቶች እየተመዘገቡ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያን ሰላምና ልማት ለማፋጠን በሚደረገው ጥረትም በበጎ ሥነ-ምግባር የታነጸ ትውልድ የመቅረፅ ኃላፊነታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም