ቀጥታ፡

ለፍትሕ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መሳካት የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ተቋማት አስተዋፅኦ የጎላ ነው

ቦንጋ፣መጋቢት 8/2018 (ኢዜአ)፦ ለፍትሕ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መሳካት የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ተቋማት ሚና የጎላ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ፍትሕ ቢሮ ገለፀ።

ቢሮው በክልሉ አስተዳደር ሥነ-ስርዓት አዋጅ፣ በባህላዊ ፍርድ ቤቶች አዋጅና በነፃ የህግ አገልግሎት ዙሪያ ከሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር በቦንጋ ከተማ መክሯል።


 

በመድረኩም የቢሮው ኃላፊ ቤተልሔም ዳንኤል እንደገለፁት በክልሉ የፍትህ ዘርፍ ትራንፎርሜሽን እቅድ ተዘጋጅቶ ከ2016 ዓ/ም ጀምሮ በመተግበር ላይ ይገኛል። 

የፍትህ ትራንስፎርሜሽን እቅዱ በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነትና ተዓማኒነት ያለው ጠንካራ ተቋም በመፍጠር የተገልጋዩን እርካታ ለማሳደግ ትልቅ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ተናግረዋል። 

የፍትህ ዘርፉ አገልግሎት አሰጣጥ ጊዜንና ጉልበትን የቆጠበ ከአድሎ፣ ከጉቦ፣ ከሙስናና ሌሎች የሥነ-ምግባር ጉድለቶች የጸዳና በቅንነት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

በፍትሕ ትራንስፎርሜሽኑ የተካተቱ 10 አምዶችን ተግባራዊ ለማድረግ የህብረተሰቡን ንቃተ ህግ ማሳደግ እና ውጤታማ የሕብረተሰብ ተሳትፎን ማረጋገጥ ወሳኝ በመሆኑ ከዚህ አንጻር የሚድያ ተቋማት ሚና የጎላ ነው ብለዋል።

የፍትህ ዘርፍ ስራዎች ወደ ህብረተሰቡ እንዲደርሱ በማድረግ ሕግ አክባሪ፣ መብቱን የሚያቅና ግዴታውን የሚወጣ የነቃ ማህበረሰብ እንዲፈጠር መገናኛ ብዙሃን ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው ነው ያሉት።

የፍትሕ ተደራሽነትና አማራጭ የግጭት አፈታት ዘዴን በመጠቀም አለመግባባቶችን በባህላዊ መንገድ መፍታት እንዲቻል በ605 ቀበሌዎች ባህላዊ ፍርድ ቤቶችን በማቋቋም አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል።

ባህላዊ ፍርድ ቤቶችን ከመጠቀም አንፃር የግንዛቤ ችግር መኖሩን ያነሱት ኃላፊዋ መገናኛ ብዙሀን ህብረተሰቡን በማስተማር ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።


 

በመድረኩ የተገኙት የክልሉ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወልደማርያም በዛብህ (ዶ/ር) የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ተቋማት በሕግና ፍትሕ ዙሪያ የህብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲሰፋና እንዲሰርፅ መስራት አለባቸው ብለዋል።

በዚህ ረገድም የተጀመሩ ስራዎችን በማጠናከር በክልሉ በሚገኙ ቋንቋዎች መረጃዎችን ተደራሽ ማድረግ ላይ በትኩረትና በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግም ገልፀዋል።

በመድረኩ የፍትሕ አካላት፣ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም