ቀጥታ፡

የጋራ ትርክትን በመገንባት ሕብረ ብሄራዊ አንድነትን ለማጠናከር የምሁራን ሚና ከፍተኛ ነው

ጎንደር፤ መጋቢት 8/2018 (ኢዜአ)፦ በህዝቦች መካከል አስተሳሳሪ ትርክትን በመገንባት ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር በሚሰራው ሥራ የምሁራን ሚና የላቀ ነው ሲሉ የአማራ ክልል ከተማና መስረተ ልማት ቢሮ ሃላፊ ሞላ መልካሙ (ዶ/ር) ገለጹ።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምሁራንና የአስተዳደር ሠራተኞች "ለሰላም ዘብ እቆማለሁ፤ የልማት አርበኛ እሆናለሁ" በሚል መሪ ሃሳብ  ከአማራ ክልልና ከጎንደር ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች ጋር ዛሬ ተወያይተዋል።


 

የቢሮው ሃላፊ  ሞላ መልካሙ (ዶ/ር) በውይይቱ ላይ እንደገለጹት በሀገራችን አስተሳሳሪና የጋራ ትርክትን በማስረጽ በህዝቦች መካከል አብሮነት እንዲጠናከር በማድረግ በኩል የምሁራን ድርሻና አበርክቶ የላቀ ነው፡፡

በህብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያ ግንባታ ላይ አተኩሮ የሚሰራ ምሁር ሀገር ትፈልጋለች ያሉት የቢሮው ሃላፊው፣ ምሁራን በምክንያታዊነት በማመን ብቃት ያለው ዜጋ ለማፍራት መስራት አለባቸው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በአስደማሚ እድገት ላይ እንደምትገኝ ጠቁመው፤ ምሁራን በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በፈጠራና በምርምር ሥራዎች እድገቱን እንዲያፋጥኑ አስገንዝበዋል።

በክልሉ በልማትና በሰላም እየተመዘገበ ያለው ውጤት መንግስት ለሰላም ካለው ቁርጠኝነት የመነጨ መሆኑን አንስተው፤ ሰላምን በዘላቂነት ለማስቀጠል በሚደረግ ጥረት ምሁራንም የመፍትሄው አካል መሆን አለባቸው ብለዋል።

"የሀገር ግንባታ ሂደቱ እንዲፋጠን ምሁራን በተሰለፉበት ሙያ እያደረጉት ያለው አበርክቶ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው" ያሉት ደግሞ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አስራት አጸደወይን (ዶ/ር) ናቸው፡፡


 

ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ሥራው ጎን ለጎን በምርምርና በማህበረሰብ አገልግሎት ችግር ፈች ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን አስታውሰው፤ ለሰላም ግንባታ ስራዎችም አጽንኦት ሰጥቶ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

ለአንድ ሀገር እድገትና ብልጽግና የምሁራን ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑንና የዩኒቨርሲቲው ምሁራንም በሀገረ መንግስት ግንባታ ታሪካዊ አሻራቸውን የሚያሳርፉበት ምቹ አውድ እንዳለ ገልጸዋል፡፡

ምሁራን በሰላምና በልማት ጉዳዮች ላይ ለሀገር የሚበጁ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በማመላከት ተሳትፏቸውን ሊያጠናከሩ ይገባል ያሉት ደግሞ የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው ናቸው፡፡ 


 

ሳይንሳዊ እውቀታቸውን በማካፈል ለከተማው እድገት መፋጠን ሃላፊነታቸውን ሲወጡ መቆየታቸውን ጠቁመው፣ ዛሬም ሀገራቸውን በቅንነትና በታማኝነት በማገልገል የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ ከተሳተፉት የዩኒቨርሲቲው ምሁራንና ሠራተኞች መካከል አቶ አረጋ ወጨፎ እንዳሉት በተሰለፉበት ሙያ ለሀገራቸው እድገት አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ።

ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ መምህር ሰለሞን ታደለ በበኩላቸው በስነ ምግባር የታነጹና በእውቀት የተካኑ ዜጎችን በማፍራት በኩል የምሁራን ድርሻና አበርክቶ ከፍ ያለ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ዘመን ተሻጋሪ መልካም እሴቶችን በአሁኑ ትውልድ ላይ በማስረጽ ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ ተግተው እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።  

በውይይት መድረኩ ላይ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም