የድንች ምርታማነትን በጥናትና ምርምር በማስደገፍ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የድንች ምርታማነትን በጥናትና ምርምር በማስደገፍ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 8/2018 (ኢዜአ)፦ የድንች ምርታማነትን በጥናትና ምርምር በማስደገፍ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ውጤታማ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ከአየርላንድ የድንች ምርምር እና ልማት ማህበር ጋር በመተባበር ብሔራዊ የድንች ምርምር ልማት አውደ ጥናት አካሒዷል።
ድንች በኢትዮጵያ በአነስተኛ መሬትና በአጭር ጊዜ ከፍተኛ ምርት የሚሰጥ በመሆኑ ለምግብ ዋስትና እና ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት ቁልፍ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚ የድንች አምራች ለመሆን የሚያስችል እምቅ አቅም ያላት ሲሆን፣ በተለይም የተሻሻሉ ዝርያዎች መጨመር ምርታማነቱን በከፍተኛ ሁኔታ እየቀየረው ይገኛል።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን (ዶ/ር) በተወካያቸው ፕሮፌሰር አሊ መሐመድ አማካኝነት ባስተላለፉት መልዕክት፤ ግብርና ለምግብ ሉዓላዊነት፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ እንዲሁም ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ተኪ የሌለው ዘርፍ መሆኑን ጠቁመዋል።
መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ልዩ ትኩረትም ከፍተኛ ለውጥ እየተመዘገበ መሆኑን አንስተዋል።
ድንች ከአገር ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ ማግኛ አማራጭ እየሆነ መምጣቱን ጠቅሰው ለምርቱ እሴት በመጨመር ረገድ በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ንጉሴ ደቻሳ በበኩላቸው፤ ምርታማነትን ማሳደግ የኢንስቲትዩቱ ዋነኛ ተልዕኮ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዚህም በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰው ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ምርምሮች የተሻሻሉ የድንች ዝርያዎችን ቁጥር ወደ 45 ከፍ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት አማካይ የድንች ምርታማነት በሄክታር 230 ኩንታል መድረሱን ተናግረው ምርቱ ሳይበላሽ ለረጅም ጊዜ የሚቆይበትን ቴክኖሎጂ ማስፋፋትና በአለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆን እሴት የመጨመር ሥራ ላይ ትኩረት ይደረጋል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የአየርላንድ ኤምባሲ ምክትል የተልዕኮ ኃላፊ ፈርጋን ሪያን በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በድንች ምርታማነት ላይ እያሳየችው ያለው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ገልጸው፣ አገራቸው በግብርናው ዘርፍ ያላትን አጋርነት አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።