ቀጥታ፡

የጤና ስርዓቱን ለማሻሻል የተከናወኑ ተግባራት ውጤት እያመጡ ነው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 8/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያን የጤና ስርዓቱን ለማሻሻል የተከናወኑ ተግባራት ውጤት እያመጡ እንደሚገኙ የጤና ዘርፍ ተመራማሪዎች ገለጹ።

መጋቢት 6/2018 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የነበረው የኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ማህበር 37ኛ ዓመታዊ ጉባኤ ዛሬ ይጠናቀቃል።

በጉባኤው ማስጀመሪያ ላይ የኢትዮጵያን የጤና ሥርዓት ለማዘመን በሚደረጉ ጥረቶች ውጤታማ የጥናትና ምርምር ላደረጉ ሙያተኞች የዕውቅና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ ተሸላሚ የጤና ተመራማሪዎች እንዳሉት፤ የጤና ስርዓቱን ለማሻሻል የተከናወኑ ተግባራት ውጤት እያመጡ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያን የጤና ሥርዓት ለማዘመን በተደረጉ ጥረቶች ላበረከቱት የጥናትና ምርምር ሥራ የተሰጣቸው ዕውቅናም ለቀጣይ ሥራ ተጨማሪ ኃላፊነትን የወሰዱበት መሆኑን ገልጸዋል።

የጂማ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ሳይንስ መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ተፈራ በላቸው፤ የጤናውን ዘርፍ ለማሻሻል በሚደረጉ ጥረቶች ውስጥ የሙያተኞች የጥናትና ምርምር ውጤት ወሳኝ ናቸው ብለዋል።

በዚህም ከ400 በላይ የጥናትና ምርምር ውጤቶችን በማበርከት በአጣዳፊ የምግብ እጥረትና ከጉሮሮ ካንሰር ጋር የተያያዙ የፖሊሲ ግብዓትነት ጥቅም ላይ መዋላቸውን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅትም የመጀመርያ ደረጃ የጤና አገልግሎት የሰው ሃብት ልማትና ተደራሽነትን የሚያጠናክሩ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን እየሰሩ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በቀጣይም የጤና መረጃ ትክክለኛነትን የሚያዘምን የጥናትና ምርምር እንደሚካሂዱ አረጋግጠዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ሰብለወርቅ መኮንን በበኩላቸው፤ የተበረከተላቸው የዕውቅና ሽልማት ለቀጣይ ሥራ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ነው ብለዋል።

በቀጣይም የኢትዮጵያን የጤና ሥርዓት ለማዘመን በሚደረገው ጥረት ከአካባቢ ብክለትና ከካንሰር በሽታ መከላከል ጋር የተያያዙ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህርና በቤልጂየም ዩኒቨርሲቲ የ3ኛ ዲግሪ ተማሪና ተመራማሪ መስከረም ዲሶ፤ ከዚህ ቀደም ለጤና ዘርፍ መዘመን አቅም የሚሆኑ ከ21 በላይ የጥናትና ምርምር ሥራ ማበርከታቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይም በቴክኖሎጂ የተደገፉ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በማፍለቅ ለጤና ሥርዓት እድገት በትኩረት እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም