ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063ን ለማሳካት ጉልህ ሚና አላቸው

ሀዋሳ ፤መጋቢት 8/2018(ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ እያከናወነች የምትገኘው ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063ን ለማሳካት ጉልህ ሚና አላቸው ሲሉ የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተናገሩ።

ፕሮጀክቶቹ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063ን ለማሳካት በጥሩ ጎዳና ላይ ስለመሆኗን የሚያሳዩ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና ተመራማሪ ንጉስ በላይ (ዶ/ር) እንደገለጹት ኢትዮጵያ በብዙ ውጣ ውረዶች ውስጥ ሆና ትልልቅ የልማት ስኬቶችን እያስመዘገበች ትገኛለች።

በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች ሀገሪቱን ተጠቃሽ እንድትሆን የሚያደርጉ መሆናቸውን ገልጸው፣ በተለይ ግዙፍ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካ መጻኢ ጊዜ ምቹ መደላድል እንደሚፈጥሩ ተናግርዋል።

እነዚህ ግዙፍ የልማት ተግባራት የአፍሪካ የ2063 የልማት አጀንዳዎችን ለማሳካትና ኢትዮጵያንም ተጠቃሽ ሀገር ለማድረግ የሚያስችሉ መሆናቸውንም ነው ንጉስ (ዶ/ር) ያነሱት።

በተለይም ኢትዮጵያ በችግር ውስጥ ሆና የውስጥ አቅሟን በማስተባባር ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ለማሳካት ያሳየችው ቁርጠኝነት የሀገሪቱን የቆየ የድህነት ታሪክ ከመቀየር ባለፈ የሥራ ዕድል ፈጠራና ዓለም አቀፍ የስበት አቅምን ያሳድጋል ብለዋል።

እንደ ንጉስ (ዶ/ር) ገለጻ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያሉትን የልማት ፀጋዎች በአግባቡ በመጠቀም ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የውስጥ ሰላምና አንድነትን ማጠናከር ይገባል።


 

"ኢትዮጵያ ከቀጣናው ባለፈ አፍሪካን ለማስተሳሰር የሚያስችል የልማት ሥራዎችን እያከናወነች ነው፤ ለዚህም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ማንሳት ይቻላል" ያሉት ሌላው ምሁር ደግሞ በሀዋሳ ዩኒቨርሰቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ምህረት ደናንቶ (ዶ/ር) ናቸው።

ኢትዮጵያ ዜጎቿን በማስተባበር በውስጥ አቅሟ የገነባችው የሕዳሴው ግድብ የቀጣናውን ሀገራት በኤሌክትሪክ ሀይል እንዲተሳሰሩ ማድረጉን አንስተዋል።

የአጀንዳ 2063 ግቦች አንዱ በልማት የተሳሰረች አፍሪካን መፍጠር መሆኑን አንስተው፣ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የጀመረቻቸው ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ይህን የሚያሳኩና ሀገሪቱንም በምሳሌነት የሚያስጠቅሱ ናቸው ብለዋል።

የሀይል አቅርቦት፣ መንገድና ሌሎች መሰረተ ልማቶች የአፍሪካ ሀገራትን በማስተሳሰር በኩል ጉልህ ሚና አላቸው ያሉት ምህረት (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ ራሷን ከድህነት የማውጣትና አፍሪካን የማስተሳሰር አጀንዳ ይዛ እየሰራች መሆኑንም ተናግረዋል።

አጀንዳ 2063ን ለመተግበር ኢትዮጵያ በጥሩ እንቅስቃሴ ላይ መሆኗን ገልጸው፣ በኢትዮጵያ የተጠናቀቁትን ጨምሮ በቅርቡ የተጀመሩ ሌሎች ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቁ ሀገሪቱን የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማዕከል ለማድረግ የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል።

ሁሉን አቀፍ በሆነ እድገት አህጉራዊ ብልጽግናን ማምጣት፣ የተሳሰረና ፖለቲካዊ አንድነት ያለው አህጉር እውን ማድረግ፣ የልማት ትስስር መፍጠርና ዘላቂ ሰላምን ማስፈን ከአፍሪካ አጀንዳ 2063 ዓላማዎች መካከል ይጠቀሳሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም