ቀጥታ፡

መንግሥት ሁሉንም የሃይማኖት ተቋማት በእኩልነት እንደ ዕሴቶቻቸውና አስተምህሯቸው በፍትሃዊነት ያገለግላል-ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤መጋቢት 8/2018(ኢዜአ)፦ መንግሥት ሁሉንም የሃይማኖት ተቋማት በእኩልነት እንደ ዕሴቶቻቸውና አስተምህሯቸው በፍትሃዊነት ያገለግላል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፥ ከሌሎች የሀይማኖት ተቋማት ጋር እንዳደረግነው ሁሉ ዛሬ ከኢትዮጵያ ወንጌላውያን፣ከካቶሊክ እና ከሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተክርስቲያናት መሪዎች ጋር “የሃይማኖት ተቋማት በመደመር መንግሥት እይታ” በሚል መሪ ሀሳብ ፍሬያማ ውይይት አካሂደናል ብለዋል።


 

በዚህም ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት፣የካቶሊክ እና የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተክርስቲያን በሰላም፣በልማትና በትውልድ ግንባታ ሂደት ውስጥ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እንዲዳብር፣አንድነት እንዲጠነክር፣ትውልድ እንዲማር፣በስነምግባር እንዲታነፅ ፣ ታሪክንና ቅርስን በመጠበቅ እንዲሁም ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ ሚና አበርክተዋል።

በተጨማሪም ቴክኖሎጂን ወደ ሀገር በማስገባትና የሥራ ባሕልን በማበረታታት ረገድ ከሌሎች የሀይማኖት ተቋማት ጋር በመሆን ወሳኝ አስተዋጽኦ አበርክተዋል ነው ያሉት።

በታሪክ ብቻ ሳይሆን ባለፉት የለውጥ ዓመታትም ተቋማቱ በከተማችን ሁለንተናዊ የሰላም ግንባታ፣የልማት እና የብልጽግና ጉዞ ላይ እያበረከቱት ያለው ተሳትፎ ጉልህ ነው።

በመድረኩ ለሕዝቦች ትስስር መጎልበት፣ በማኅበራዊ ልማትና በበጎ ፈቃድ ሥራዎች ተሳትፎ፣ የሥራ ባሕልን በማስረጽ፣ ትውልድን በሥነ ምግባር በመገንባት፣ የበጎነት ስራ መስራት እንዲለመድ በማድረግ፣ለመልካም አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ መጎልበት እንዲሁም ሰላምን በማስፈንና ሕገወጥነትን በመከላከል ረገድ ለኢትዮጵያ ብልጽግና እና ለብሔራዊ ጥቅም በጋራ ለመቆም ጠቃሚ ውይይት ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።


 

በውይይታችን የተነሱ በስራ ሂደት ያጋጠሙ አንዳንድ ክፍተቶችን እና እንግልቶችን በቀጣይ በትብብር ለማረም የሚያስችል ምቹ መደላድል የፈጠረ ውጤታማ መድረክ እንደነበርም ገልጸዋል።

ይህ መድረክ በየክፍለ ከተማው ሲካሄዱ የቆዩ ውይይቶች ማጠቃለያ ሲሆን፣ የመንግሥትንና የሃይማኖት ተቋማትን ሚና እና ድርሻ በግልጽ ለይቶ ያስቀመጠ ነው ብለዋል።

የወንጌላውያን፣የካቶሊክ እና የኢትዮጵያ የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተክርስቲያን መሪዎች ላደረጋችሁት ከፍተኛ ተሳትፎና ለሰጣችሁት ገንቢ ሐሳብ በራሴና በከተማ አስተዳደሩ አመስግነዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም