ቀጥታ፡

በወሰድነው የምርጫ ካርድ ዴሞክራሲያዊ ተሳትፏችንን እናረጋግጣለን

ጎንደር፤ መጋቢት 8/2018 (ኢዜአ)፡-ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ተመዝግበው በወሰዱት የምርጫ ካርድ ዴሞክራሲያዊ ተሳትፏቸውን እንደሚያረጋግጡ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

ወጣት ዮሃንስ ቸኮል፣ ለመራጭነት የሚያበቃውን ካርድ ቀድሞ ማውጣቱ በእለቱ የሚፈልገውን ፓርቲ ለመምረጥ እንደሚያስቸለው ተናግሯል።

"በሀገራችን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ስር እንዲሰድ በምርጫ ተሳትፎ ማድረግ ወሳኝ ነው" ያለው  ወጣት ዮሃንስ በምርጫው የነቃ ተሳትፎ ለማድረግ መዘጋጀቱን ገልጿል፡፡

ምርጫ ካርድ የወሰዱት ወይዘሮ ፈንታነሽ ሙላት በበኩላቸው ለሴቶች ተጠቃሚነትና መብት መረጋገጥ በግንባር ቀደምነት የሚታገል ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡

ሴቶች ወደ አመራር ቦታ እንዲመጡ ዴሞክራሲያዊ መብታችንን ተጠቅመን በምርጫው የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል።፡

የቅድመና ድህረ ምርጫው ሂደትና ውጤቱ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና በህዝብ ዘንድ ተዓማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉ ገልጸዋል።

ወይዘሮ የሺወርቅ ባያብል በበኩላቸው ሴቶች  ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን በመጠቀም ለሀገራችን ዘላቂ ሰላምና ልማት መረጋገጥ ተግቶ የሚሰራ ፓርቲን በመምረጥ ረገድ ተሳትፏቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በመጪው ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚካሄድ የምርጫ ቦርድ ካወጣው መርሃ ግብር መረዳት ተችሏል። 

ምርጫውን በስኬት ለማጠናቀቅም አሁን ላይ የመራጮች ምዝገባና ሌሎች የቅድመ ምርጫ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም