ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ብሔራዊ ጥቅምን የማስጠበቅ ጉዳይ በመሆኑ ያለ ልዩነት እንደግፈዋለን - የፖለቲካ ፓርቲዎች

ቦንጋ፤ መጋቢት 8/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ብሔራዊ ጥቅምን የማስጠበቅ ጉዳይ በመሆኑ ያለልዩነት እንደሚደግፉትና ምላሽ እስኪያገኝ የበኩላቸውን እንደሚወጡ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።

በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች፤ የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄ ብሔራዊ ጥቅምን የማስጠበቅ ጉዳይ በመሆኑ ያለልዩነት እንደግፈዋለን ብለዋል።

የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮቹ ብሔራዊ ጥቅምን የማስከበር ጉዳይ አንገብጋቢ አጀንዳ ስለሆነ የባህር በርን ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት ሁላችንም ልንደግፍ ይገባል ብለዋል። 

በክልሉ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ ተወካይ አቶ ሰለሞን መኮንን እንዳሉት የሀገር ጥቅም ለድርድር የማይቀርብ ከሁሉም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው  ነው።


 

የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ ለአንድ ወገን ብቻ የሚተው ሳይሆን የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ተሳትፎና የጋራ አቋም የሚፈልግ እንደሆነ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በስህተት ያጣችውን የባህር በር ለማግኘት እያደረገቸው ያለው እንቅስቃሴ የዚሁ አካል በመሆኑ ፓርቲያቸውም ይህን ጉዳይ በማኒፌስቶው ውስጥ አካቶ እየሰራበት እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የራሳችን ሀብት የሆነውን የባህር በር መልሶ ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊደግፈው ይገባል ብለዋል።

በተለይም የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀገር የሁሉም  መሠረት በመሆኗ ብሔራዊ ጥቅሟን ማስጠበቅና ዳር ድንበሯን ማስከበር ላይ የጋራ አቋም ሊይዙ እንደሚገባም አመልክተዋል።

የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ የክልሉ ተወካይ አቶ ሀይሉ ተስፋዬ በበኩላቸው የባህር በር ጉዳይ ለድርድር የማይቀርብ ቀዳሚ አጀንዳ መሆኑን ገልጸዋል፡፡


 

ፓርቲያቸውም ለጉዳዩ ልዩ ቦታ ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ጠቅሰው አሁን የተጀመረው የዲፕሎማሲ ጥረት ውጤታማ ይሆናል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

የባህር በር ለማግኘት የተነሳው ጥያቄ የትውልዱ ጥያቄ መሆኑን በመገንዘብ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

የባህር በር ለኢትዮጵያ የእድገትና የብሔራዊ ደህንነት ጉዳይ መሆኑን የገለፁት የሞቻ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ሞዴፓ) ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አዲሱ አምበሎ በመንግስት የተጀመረው ጥረት የሚበረታታ እንደሆነና ፓርቲያቸውም በፅኑ አቋም እንደሚደግፈው አረጋግጠዋል። 


 

ከሚለያዩን ነገሮች ይልቅ አንድ የሚያደርጉን ጉዳዮች በርካታ ናቸው ያሉት አቶ አዲሱ አምበሎ፣ ችግሮችን በውይይት እየፈቱ  በሀገር ጉዳይ ላይ በጋራ መቆም ከሁሉም የሚጠበቅ ተግባር ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም