ቀጥታ፡

የሎጂስቲክስ ሉዓላዊነታችንን በራስ አቅም የማረጋገጥ አዲስ ምዕራፍ ላይ ነን - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 8/2018(ኢዜአ) የሎጂስቲክስ ሉዓላዊነታችንን በራስ አቅም የማረጋገጥ አዲስ ምዕራፍ ላይ ነን ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ዛሬ በእንዶዴ ደረቅ ወደብ ማስፋፊያ እና በኤኤምጂ (AMG) - እንዶዴ የባቡር መሥመር ፕሮጀክቶች ላይ ያደረግነው ምልከታ፤ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሪፎርም በጠንካራ መሠረት ላይ እየቆመ ለመሆኑ በተግባር ያረጋገጠ ነው ብለዋል።


 

የኤኤምጂ - እንዶዴ የባቡር መሥመር በሀገር በቀል የግል ኩባንያ ፋይናንስ የተደረገ የመጀመሪያው የባቡር መሠረተ ልማት ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ይሄም የግል ዘርፉ ለሀገር ግንባታ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በልዩ ትኩረት ከተያዘለት ጊዜ ቀድሞ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑም "ዐቅዶ መጀመር፣ ጀምሮ መፈጸም" የሚለውን መርሐችንን ያጸና ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ይህ የሦስት ኪሎ ሜትር ባቡር መሥመር በገላን ኢንዱስትሪ ዞን የሚመረቱ ምርቶችን ቡናን ጨምሮ በቀጥታ ከባቡር መሥመሩ ጋር በማገናኘት፣ ምርቶች በፍጥነትና በተወዳዳሪ ዋጋ ለዓለም ገበያ እንዲቀርቡ ያስችላል ብለዋል።


 

የእንዶዴ ደረቅ ወደብ ማስፋፊያ የኮንቴነር ማከማቻ ዐቅምን 5 እጥፍ ሲያሳድግ፤ የጭነት የማውረድና የመጫን መጫኛ ጊዜን 10 ሰዓት ወደ ሁለት ሰዓት ዝቅ በማድረግ የንግድ ሥርዓታችንን ያዘምናል፤ ፈጣን የሎጂስቲክስ አገልግሎትን ይፈጥራል ነው ያሉት በመልዕክታቸው።

እነዚህ በራስ ዐቅም የሚገነቡ መሠረተ ልማቶች የሎጂስቲክስ ተወዳዳሪነታችንን ከማሻሻል ባለፈ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነታችንን ያጸናሉ ሲሉም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን የአፍሪካ የንግድና የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ የምናደርገውን ጉዞ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም