ቀጥታ፡

ዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም የአርሶ አደሩን አቅም ለማሳደግና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ትኩረት ተደርጓል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 8/2018(ኢዜአ)፦ ዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም የአርሶ አደሩን የፋይናንስ አቅም ማሻሻልና የግብርና ግብዓቶች ተጠቃሚነትን ማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሺእመቤት ነጋሽ ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን እና የግሪን አግሮ ሶሉሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ "ለእርሻ" በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመዋል።

ኢትዮጵያ የሀገራትን ዕጣ ፈንታ በሚወስነው የዲጂታል ዘመን ደጃፍ ላይ ትገኛለች

ስምምነቱን የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሺእመቤት ነጋሽ እና የግሪን አግሮ ሶሉሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ "ለእርሻ" ሥራ አስፈፃሚ አብረሃም እንዲሪያስ ተፈራርመዋል።

ስምምነቱ የዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም አርሶ አደሮችን የፋይናንስ አቅም ለማሻሻልና የግብርና ግብዓቶች ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ያለመ እንደሆነ ተመልክቷል።


 

የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሺእመቤት ነጋሽ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት ኮርፖሬሽኑ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመንና ምርታማነትን ለመጨመር እየሰራ ይገኛል። 

ስምምነቱ አርሶ አደሩ የግብርና ግብዓቶችን፣ የፋይናንስ አገልግሎቶችንና የሜካናይዜሽን አማራጮችን በቀላሉ ማግኘት የሚችልበትን መንገድ ለመፍጠር ያለመ ነው ብለዋል።

በዚህም መሰረት ብሔራዊ የግብርና ፍኖተ ካርታ እና ፋይናንስ አካታችነት ትግበራ ላይ በጋራ በመስራት እስከ 2030 ድረስ ለአንድ ሚሊየን አነስተኛ አርሶ አደሮች የብድር እድል ለማመቻቸት የተያዘውን እቅድ ለማሳካት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የአርሶ አደሮችን መረጃ በዲጂታል በማደራጀትና ለፋይናንስ ተቋማት ግልጽነት ያለው መረጃ በመስጠት ብድር የሚመቻችበት ሁኔታ እንደሚፈጥርም አንስተዋል።

ኮርፖሬሽኑ የእርሻ ማሽነሪዎችን፣ መለዋወጫዎችንና የቴክኒክ ስልጠናዎችን እንደሚያቀርብ ጠቁመው "ለእርሻ" በበኩሉ በዲጂታል የታገዘ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በመዘርጋት አርሶ አደሮችና ወጣቶች ማሽነሪዎችን እንዲገዙ ወይም እንዲከራዩ ያመቻቻል ብለዋል።

ሁለቱ ተቋማት የአየር ሁኔታ ምክር፣ የግብዓት አቅርቦት እና ዲጂታል የኮንትራት እርሻ አገልግሎቶችን በመተግበር የሀገሪቱን የዲጂታል ግብርና ፍኖተ ካርታ እንደሚያፋጥን ጠቅሰዋል።

አርሶ አደሮች የሚፈልጓቸውን አግሮ-ኬሚካሎች፣ ምርጥ ዘር እና ማዳበሪያ "ለእርሻ" ቀድሞ ፍላጎት በመሰብሰብ ለኮርፖሬሽኑ በማቅረብ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ይሰራል ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሃብታሙ ሃይለሚካኤል በበኩላቸው ኢትዮጵያ ሰፊ የግብርና ፀጋ ያላት ሀገር መሆኗን ጠቁመው ይህን እምቅ ሀብት ወደ ተጨባጭ ውጤት ለመቀየር ቴክኖሎጂ መጠቀም ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

የቴክኖሎጂ ግብዓት አጠቃቀምን በማስፋት እና ግብርናውን በማዘመን የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥና ምርታማነትን ማሳደግ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።

ስምምነቱ በግብርናው ዘርፍ ዘመናዊ አሰራርን በማስተዋወቅና የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ በኩል ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።


 

የግሪን አግሮ ሶሉሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ "ለእርሻ" ሥራ አስፈፃሚ አብረሃም እንዲሪያስ በበኩላቸው ስምምነቱ አርሶ አደሩ የግብርና ሥራውን በብቃት ማከናወን የሚያስችለውን የፋይናንስ አቅርቦት በቀላሉ እንዲያገኝ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም