ቀጥታ፡

የኃይማኖት ተቋማት የነገ ተስፋን የሚያለመልሙ የልማትና ሰላም ግንባታ ምሰሶ ናቸው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 7/2018 (ኢዜአ)፦የኃይማኖት ተቋማት አብሮነትን በማጠናከር የኢትዮጵያን የነገ ተስፋ የሚያለመልሙ የልማትና ሰላም ግንባታ ምሰሶ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ''የኃይማኖት ተቋማት በመደመር መንግስት ዕይታ” በሚል መሪ ሃሳብ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን አባቶችና ምዕመናን ጋር የማጠቃለያ መድረክ አካሂዷል።

በመድረኩም የመደመር መንግስት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ላይ ያለውን ምልከታ የሚዳስስ የመነሻ ፅሁፍ ቀርቦ ምክክር ተደርጎበታል።

የመድረኩ ተሳታፊ አባቶችና የእምነቱ ተከታዮችም መንግስት ቤተ-ክርስቲያኗ በምታቀርባቸው ጥያቄዎች ላይ ለሚሰጠው አፋጣኝ ምላሽ ምስጋና አቅርበዋል።


 

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በአደባባይ የሚከበሩ የአደባባይ በዓላት ኃይማኖታዊ ዕሴታቸውን ጠብቀው እንዲከበሩ በማድረግ አስደናቂ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በመዲናዋ የተገነቡ ስኬታማ የልማት ሥራዎችም የነዋሪዎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ አዲስ አበባ ውብ ገጽታ እንድትላበስ ማድረጉን ተናግረዋል።

በቀጣይነትም በአዲስ አበባ ዘላቂ የልማትና ሰላም ግንባታ ሥራ የሚጠበቅባቸውን ገንቢ ሚና እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

በተነሱ ጉዳዮች ላይ ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር ዓባይ፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በመዲናዋ አስደናቂ የልማት ውጤት ተገኝቷል ብለዋል።


 

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለሚቀርቡ ጉዳዮችም ከተማ አስተዳደሩ አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት በፍትሀዊነት እያስተናገደ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይም ጽንፈኝነትና አክራሪነትን በመታገል ለአዲስ አበባና ኢትዮጵያ የብልፅግና ጉዞ ስኬት በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን በሀገረ መንግስት ግንባታ ውስጥ የማይተካ ሚና እየተጫወተች እንደሚገኝ ገልጸዋል።


 

የመደመር መንግስትም ቤተክርስቲያኗ ትውልድን በመቅረጽ፣ ቅርስና ታሪክን በመጠበቅ ለሀገር ግንባታ ላበረከተችው አስደናቂ አስተዋጽኦ ዕውቅና እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

በቀጣይም የእምነት ተቋማት ትውልድን በመልካም ሥነ-ምግባር በመቅረፅ ለሀገር ዘላቂ ልማትና ሰላም ግንባታ የሚኖራቸውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

ከተማ አስዳደሩም የእምነት ተቋማት የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች በፍትሐዊነት ምላሽ በመስጠት የመዲናዋን ዘላቂ ሰላምና ልማት ግንባታ የማፋጠን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የኃይማኖት ተቋማት የዜጎችን ሕብረብሔራዊ አንድነት በማጠናከር የኢትዮጵያን የነገ ተስፋ የሚያለመልሙ የልማትና ሰላም ግንባታ ምሰሶ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።

ለዚህም የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና በማረጋገጥ ድህነትን ለማጥፋት በሚደረገው ርብርብ የእምነት ተቋማት ዘላቂ ልማትና ሰላምን በመገንባት ወሳኝ ድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም