ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ ልማት የአካባቢ ጥበቃን ከቱሪዝም ጋር በማስተሳሰር በአርዓያነት የሚጠቀስ ነው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 7/2018 (ኢዜአ)፦የአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ ልማት ወንዞችን አረንጓዴ በማልበስና የአካባቢ ጥበቃን ከቱሪዝም ጋር በማስተሳሰር ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በአርዓያነት የሚወሰድ መሆኑን የዛምቤዚ ወንዝ ተፋሰስ ኮሚሽን አባላት ሀገራት ተወካዮች ገለፁ።

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ለዛምቤዚ ተፋሰስ አገራት ተሞክሮ የሚሆን ነው

የዛምቤዚ ወንዝ ተፋሰስ ኮሚሽን አባል ሀገራት ተወካዮች የአዲስ አበባን የወንዝ ዳርቻ ልማት ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ወቅት የመዲናዋን የወንዞች ዳርቻ በማልማት ከቆሻሻ መጠራቀሚያነት አውጥቶ ወደ ሕዝብ መዝናኛነትና የከተማ ውበት አካል እንዲሆኑ እየተደረገ መሆኑን አድንቀዋል። 

በተለይም የወንዝ ዳርቻዎችን አረንጓዴ በማልበስ የአካባቢ ጥበቃን ከቱሪዝም ጋር የማስተሳሰር ረገድ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ትልቅ ትምህርት እንደሚሆን ገልጸዋል።


 

የዛምቤዚ ወንዝ ተፋሰስ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ፌሊክስ ሞሲ ንጋምላጎሲ፥ የአፍሪካ ከተሞች የታቀዱ፣ ሳቢ እና የቱሪስት መዳረሻዎች እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ አዲስ አበባ በአርዓያነት የምትጥቀስ ናት ብለዋል።

በተለይም አሁን ላይ በአዲስ አበባ እየታዩ ያሉ ለውጦች ከተማዋን ለሰዎች መዝናኛና ለኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ተመራጭ እያደረጓት መሆኑን ተናግረዋል።

ሌሎች የአፍሪካ ከተሞች በአዲስ አበባ እየተከናወኑ ካሉ የልማትና የከተማ ውበት ስራዎች ልምድ እንዲቀስሙና ትምህርት እንዲወስዱ ጥሪ አቅርበዋል።

ከዚምባብዌ  የመጡት ቺቶ ፊሪ በበኩላቸው፤ የአዲስ አበባ የሕዝብ መዝናኛ ፓርኮች በስፋት ተገንብተው መመልከታቸውን በአድናቆት ጠቅሰዋል።


 

ይህም ለከተማዋ ድምቀት ከመሆኑ ባለፈ ለነዋሪዎችና ለጎብኝዎች ምቹ የመንቀሳቀሻ ከባቢን የሚፈጥር ነው ብለዋል።

በአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻና የኮሪደር ልማት ለእግረኛ መንገድ የተሰጠው ትኩረት ለጤና እጅግ ተስማሚ የሆነውን የእግር ጉዞ ባህል እንደገና ለማነቃቃት ትልቅ ዕድል መፍጠሩንም ነው የተናገሩት።


 

ከሞዛቢክ የመጡት ማኑኤል ቻጉሎ፤  ከ15 ዓመታት በፊት ኢትዮጵያን ጎብኝተው እንደነበር በማስታወስ፤ አሁን ድጋሚ ሲመጡ አዲስ አበባ አስድናቂ ለውጥና ዕድገት አስመዝግባ እንዳገኟት ተናግረዋል።

ከዚህም ባለፈ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት ልምድ የሚቀሰምበት ተጨባጭ  ለውጥ ማምጣቷን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም