የዜጎችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተመዘገቡ ውጤቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የዜጎችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተመዘገቡ ውጤቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 7/2018 (አዜአ)፦ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪት የዜጎችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተመዘገቡ ውጤቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብት ልማት፣ ሥራ ሥምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።
በምክር ቤቱ የሰው ሃብት ልማት፣ ሥራ ሥምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴርን የስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ገምግሟል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል፤ የ2018 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን አቅርበዋል።
በሪፖርታቸውም፤ ባለፉት ስድስት ወራት በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪት ኢንተርፕራይዞችንና የመዳረሻ ሀገራትን በማስፋት ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር እንደተቻለ ገልጸዋል።
በዚህም በሀገር ውስጥ ለ2 ነጥብ 7 ሚሊየን ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር በተያዘው ዕቅድ መሰረት በብዝኅ ኢኮኖሚ ዘርፎች ውስጥ 2 ነጥብ 8 ሚሊየን ዜጎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አስታውቀዋል።
የቋሚ ኮሚቴው አባላትም፤ ባለፉት ስድስት ወራት የዜጎችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራትንና የቀጣይ ስራዎችን በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን ሶካ፤ የኢንተርፕራይዞችን የፋይናንስ ፍላጎት ምላሽ መስጠት የሚያስችል አሰራር በመዘርጋት ዜጎችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ እየተቻለ ነው ብለዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ዳንኤል ተሬሳ፤ የመዳረሻ ሀገራትን በማስፋት ዜጎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በሂደቱም በውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪት ወቅት ሕጋዊ ግዴታቸውን በማይወጡ ኤጄንሲዎች ላይ ሕጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ እየተወሰደ ነው ብለዋል።
የቴክኒክና ሙያ ተቋማት በዕውቀትና ክህሎት የበለጸገ ዜጋ በማፍራት ለሥራ ገበያው ዝግጁ የሆነ የሰው ሃይል እያቀረቡ ነው ያሉት ደግሞ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በሬቻ (ዶ/ር) ናቸው።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል፤ በበጀት ዓመቱ ቀሪ ወራት የክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል ግንባታን በማጠናቀቅ ዕውቀትና ክህሎትን ያጣመሩ ዜጎች ለማፍራት በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር)፤ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪት የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራት እያከናወነ ነው ብለዋል።
በቀጣይም ዘመናዊ የቴክኖሎጂ አቅምን የበለጠ በማጠናከር ዜጎች በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪት ተጠቃሚነትን ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።