ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና ጣልያን አጋርነታቸውን ለማጠናከር የጋራ ቁርጠኝነታቸውን ገለጹ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 7/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና ጣልያን ያላቸውን የረጅም ጊዜ አጋርነት ይበልጥ ለማጎልበት እንደሚሰሩ አስታወቁ።

በገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ የተመራ ልዑክ የኢትዮጵያ እና ጣልያን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር ያለመ ጉብኝት በጣልያን ሮም እያደረገ ይገኛል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ከጣልያን የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ምክትል ሚኒስትር ኤድሞንዶ ቺሬሊ ጋር ተወያይተዋል።

ውይይቱ ኢትዮጵያ እና ጣልያን የኢኮኖሚ ትብብር፣ የልማት አጋርነት፣ የግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንትና ቀጣናዊ መረጋጋት ላይ ያላቸውን ትስስር ማስፋት ላይ ያተኮረ ነው።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ ያለበትን ደረጃ አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል።


 

በተጨማሪም የኢኮኖሚ መረጋጋትን ዘላቂ ለማድረግ፣ የኢንቨስትመንት ምህዳርን ለማሻሻልና ሁሉን አካታች እድገትን ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን በተመለከተም ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የጣልያን የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ምክትል ሚኒስትር ኤድሞንዶ ቺሬሊ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ለውጥ ያደነቁ ሲሆን በቀጣናው መረጋጋት ያላትን ሚና አንስተዋል።

ምክትል ሚኒስትሩ ጣልያን በጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ አማካኝነት የኢትዮጵያን የልማት የትኩረት መስኮች ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኗንም አረጋግጠዋል።

ሁለቱ ወገኖች በውይይታቸው ኢትዮጵያ እና ጣልያን ያላቸውን የረጅም ጊዜ አጋርነት የበለጠ ለማጠናከር መስማማታቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መረጃ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም