ቀጥታ፡

ቤተክርስቲያኗ በከተማችን ሁለንተናዊ የልማት ጉዞ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተች ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 7/2018 (አዜአ)፡- በታሪክ ብቻ ሳይሆን ባለፉት የለውጥ ዓመታትም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተክርስቲያን በከተማችን ሁለንተናዊ የልማት እና የብልፅግና ጉዞ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተች ነው ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባዋ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ የሐይማኖት ተቋማት በመደመር መንግሥት ዕይታ በሚል መሪ ሐሳብ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተክርስቲያን የሐይማኖት አባቶችና አመራሮች ጋር ፍሬያማ ውይይት አካሂደናል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተክርስቲያን የዛሬዋን ኢትዮጵያ በመገንባት ረገድ ከሌሎች የሐይማኖት ተቋማት ጋር በመሆን ወሳኝ ሚና አበርክታለች ሲሉም ገልጸዋል።


 

ቤተክርስቲያኗ በሀገረ መንግሥት ግንባታ፤ ጥንታዊ ቅርሶችን፣ ታሪኮችንና ትውፊቶችን ጠብቆ ለትውልድ በማሸጋገር፣ ትውልድን በማነጽ፣ ግብረ-ገብነትንና ሰብዓዊ ርኅራኄን በማስተማር፣ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን በማጠናከር እንዲሁም በልማት ተሳትፎ የጎላ ድርሻ ስትወጣ ቆይታለች ብለዋል ከንቲባዋ።

በውይይቱም በታሪክ ብቻ ሳይሆን ባለፉት የለውጥ ዓመታትም ቤተክርስቲያኗ በከተማችን ሁለንተናዊ የሰላም ግንባታ፣ የልማት እና የብልፅግና ጉዞ ላይ እያበረከተች ያለውን አስተዋጽኦ አንስተናል ነው ያሉት።

ለሕዝቦች ትስስር መጎልበት፣ ለሰላም፣ ለኢትዮጵያ ብልፅግና እና ለብሔራዊ ጥቅም በጋራ ለመቆም መግባባት ላይ ደርሰናልም ብለዋል።

በውይይት መድረኩ የተነሱ አንዳንድ ያጋጠሙ ክፍተቶችን በትብብር ለማረም የሚያስችል ምቹ መደላድል የፈጠረ ውጤታማ መድረክ ነበር ሲሉም ገልጸዋል።

መድረኩ በየክፍለ ከተማው ሲካሄዱ የቆዩ ውይይቶች ማጠቃለያ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ይህም የመንግሥትን እና የሐይማኖት ተቋማትን ሚና ብሎም ድርሻ በግልጽ ለይቶ ያስቀመጠ መሆኑንም አመላክተዋል።

የኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተክርስቲያን አባቶችና አመራሮች ላደረጋችሁት ከፍተኛ ተሳትፎና ገንቢ ሐሳብም አመስግነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም