ቀጥታ፡

የወረዳው አርሶ አደሮች በበልግ ወቅት እርሻ ስራ ውጤታማ ለመሆን በትጋት እየሰሩ ነው

ሀላባ ቁሊቶ ፤መጋቢት 7/2018 (ኢዜአ):- በበልግ ወቅት እርሻ ስራ ውጤታማ ለመሆን ጠንክረው እየሰሩ መሆኑን በሀላባ ዞን የዌራ ዲጆ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ።

የሀላባ ዞን ግብርና መምሪያ በበኩሉ በዞኑ በበልግ ወቅት እርሻ ከ39 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በማልማት ከ1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ ነው ብሏል።

በዞኑ የዌራ ዲጆ ወረዳ አርሶ አደሮች ለኢዜአ እንደገለጹት፤ እየጣለ ያለውን ዝናብ በአግባቡ ተጠቅመው በበልግ ወቅት እርሻ ውጤታማ ለመሆን ጠንክረው እየሰሩ ነው፡፡

በዞኑ የዌራ ዲጆ ወረዳ የሲንብጣ ቀበሌ አርሶ አደር ጀማል ሀሰን በበልግ እርሻ በ1 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ በቆሎ፣ ስንዴ፣ ዳጉሳና ሌሎችን ለመዝራት አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም አሁን ላይ እየጣለ ያለውን ዝናብ በአግባቡ ለመጠቀም መሬትን ደጋግሞ በማረስ ውጤታማ ለመሆን እየሰሩ እንዳለ ጠቅሰው ለዚሁ የሚሆን ዘርና ማዳበሪያ ማግኘታቸውንም ገልጸዋል።

በወረዳው የበሸኖ ቀበሌ አርሶ አደር ሀቢብ ጉጄ በበኩላቸው ባላቸው ከ2 ሄክታር በላይ ማሳ የበልጉን ዝናብ በመጠቀም በቆሎና ቦሎቄ ለመዝራት ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የዘንድሮው የበልግ ዝናብ ቀድሞ መግባቱ የበለጠ እንዳነሳሳቸው ጠቅሰው የተሻለ ምርት ለማግኘት የተፈጥሮ ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘርና ሌሎች ግብዓቶችን በመጠቀም ዝግጅት እያደረጉ እንደሆነ ተናግረዋል።

የሚያመርቱትን ምርት ከቤት ፍጆታ ባለፈ ለገበያ በማቅረብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ ለመሆን በግብርና ባለሙያዎች ድጋፍ ታግዘው እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

በወረዳው በበልግ ከ10 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች በኩታ-ገጠም ለመሸፈን ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን ያነሱት ደግሞ የወረዳው የግብርና ጽህፈት ቤት ምክትልና እርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሪባቶ ቃባቶ ናቸው።

በዚህም ከ678 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ግብ መጣሉን ጠቅሰው ይህን ለማሳካትም በቂ ግብዓት መቅረቡንና የግብርና ባለሙያዎች ደግሞ በተቀናጀ መልኩ ድጋፍና ክትትል እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዞኑ በመደበኛው የበልግ ወቅት እርሻ ከ39 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በማልማት ከ1 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የሀላባ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሀጂ ኑሪዬ ናቸው ።


 

የዝናብ ውሃና እርጥበትን በመጠቀም ውጤታማ ለመሆን በተቀናጀ መንገድ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው ከ22 በላይ ቀበሌዎች እርጥበትን በመጠቀም የቅድመ በልግ እርሻ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

በዞኑ ለማልማት ከታቀደው መሬት 60 በመቶው በክላስተር እንደሚለማ የጠቀሱት ኃላፊው ይህም ቴክኖሎጂና ግብዓትን አቀናጅቶ በመጠቀም ውጤታማ ለመሆን እንደሚያግዝም አመልክተዋል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም