ቀጥታ፡

በጋሞ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ሰብአዊ ድጋፍ ከማድረግ ጎን ለጎን መልሶ ለማቋቋም በቅንጅት እየተሰራ ነው- የዞኑ አስተዳደር

አርባ ምንጭ ፤መጋቢት 7/2018 (ኢዜአ)፡-በጋሞ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ሰብአዊ ድጋፍ ከማድረግ ጎን ለጎን መልሶ ለማቋቋም በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ፡፡

አስተዳደሩ አደጋው ከተከተበት ጊዜ አንስቶ ለተጎዱ ወገኞች በተለያየ መንገድ ድጋፍ ያደረጉ አካላትንም አመስግኗል፡፡

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ደምስ አድማሱ (ዶ/ር) ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፣ በዞኑ በተለያዩ ወረዳዎች በተከሰተ የመሬት መንሸራተት አደጋ በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል።

በዚህም የሰው ህይወት መጥፋቱንና ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ወገኖች በጊዜያዊ መጠለያ እንደሚገኙ ገልጸው፣ለተጎጂዎች ሰብአዊ ድጋፍ ከማድረግ ጎን ለጎን  መልሶ ለማቋቋም በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደን ጨምሮ በየደረጃው ያሉ የሥራ ሃላፊዎች ተጎጂዎችን ከማጽናናት ባለፈ በቀጣይ ለሚሰሩ ሥራዎች በቅርበት እየደገፉ መሆኑንም ገልጸዋል።

በእስካሁኑ ሂደት በየደረጃው ያሉ የመንግስት መዋቅሮችን ጨምሮ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ባለሃብቶች ላደረጉት ሰብአዊ ድጋፍም  ደምስ (ዶ/ር) አመስግነዋል፡፡

የዞኑ አስተዳደር ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም ከክልል እስከ ፌደራል ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው ፣ ድጋፉ ቀጥታ ለተጎጂዎች እንዲደርስም በልዩ ትኩረት እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ለወገን ደራሽ ወገን በመሆኑ በመልሶ ማቋቋም ሥራው በሀገር ውስጥና በውጭ ያሉ ወገኖች ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

የአካባቢው መልክዓ ምድር አቀማመጥ ለትራንስፖርት አዳጋች ቢሆንም የተለያዩ የማጓጓዣ አማራጮችን በመጠቀም  ድጋፉን ለተፈናቃይ ወገኖች የማድረስና የመንገድ ጥገና ስራም እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚደረግ ሰብአዊ ድጋፍና መልሶ የማቋቋም ሥራ በቅንጅት እየተከናወነ መሆኑ መግለጻቸውም ይታወሳል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም