በሐረሪ ክልል ህገ-ወጥ የነዳጅ ግብይትን በሚፈጽሙ ማደያዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ ይወሰዳል - ኢዜአ አማርኛ
በሐረሪ ክልል ህገ-ወጥ የነዳጅ ግብይትን በሚፈጽሙ ማደያዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ ይወሰዳል
ሐረር፤ መጋቢት 7/2018 (ኢዜአ)፡- በሐረሪ ክልል ህገ ወጥ የነዳጅ ግብይትን በሚፈጽሙ ማደያዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ የክልሉ ኢንተርፕራይዞች ልማትና ኢንዱስትሪ ቢሮ አስታወቀ።
ነዳጅን በቁጠባ፣ ለመሠረታዊ ነገሮች ቅድሚያ በመስጠት በኃላፊነት ስሜት መጠቀም እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዛሬ ማሳሰባቸው ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የነዳጅ አከፋፋዮች፣ ማደያዎች እና ሌሎች ተጠቃሚዎች ነዳጅን በቁጠባ እንዲጠቀሙ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ይህንንም በተመለከተ ቢሮው በሐረሪ ክልል በነዳጅ ግብይት ላይ የሚስተዋሉ ህገ-ወጥ ተግባራትን መከላከል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።
የክልሉ ኢንተርፕራይዞች ልማትና ኢንዳስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማኢል ዩስፍ እንደተናገሩት፤ በክልሉ ህገ-ወጥ የነዳጅ ግብይትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ግብረ ሃይል ተቋቁሞ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።
በመሆኑም መንግስት በከፍተኛ ድጎማ ወደ ሀገር የሚያስገባውን ነዳጅ ለመሰረታዊ ጉዳይ ከማዋል ይልቅ በአቋራጭ ለመበልጸግ በሚሹ አካላት የሚደረጉ ህገ- ወጥ ተግባራትን ለመከላከል በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በተለይ ከነዳጅ ማደያ ውጪ ግብይት የሚፈጽሙ፣ ከተቀመጠው ታሪፍ በላይ የሚሸጡ እና ሌሎች ተያያዥ ህገ-ወጥ ተግባራት የሚያከናውኑ የነዳጅ ማደያዎች መኖራቸው እንደተደረሰበት አንስተዋል።
እንዲሁም አንዳንድ ማደያዎች የነዳጅ ምርትን በሕጋዊ ሥርዓት እንዳይሰራጭ በማድረግ ሕገ-ወጥ ተግባር እንደሚፈጽሙ አንስተዋል።
ደንበኞችን በማጉላላት ህገ-ወጥ የነዳጅ ግብይት የሚፈጽሙ አካላት መኖራቸውን ጠቁመው በዚህ እና መሰል ተግባራት ላይ የተሰማሩ የነዳጅ ማደያዎች ከድርጊታቸው በመቆጠብ ህግና መመሪያን አክብረው እንዲሰሩ አሳስበዋል።
ከተቀመጠው አሰራር ውጪ ሲተገብሩ በሚገኙ የነዳጅ ማደያዎች ላይ ጠንካራ፣ ህጋዊና አስተዳደራዊ የእርምት እርምጃ እንደሚወሰድም አስጠንቅቀዋል።
የሐረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር አህመድ አብዲ በበኩላቸው፤ በክልሉ በነዳጅ ግብይት ላይ የሚከናወኑ ህገ-ወጥ ግብይትና ሌሎች ተያያዥ ተግባራትን የመከታተልና የመቆጣጠሩ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በዚህም በዘርፉ የተሰማሩ አካላት በአግባቡ ግብይት ሊፈፅሙ እንደሚገባ ጠቁመው በተለይ የትብብርና ቅንጅት አሰራሮችን ማጠናከር እንደሚገባም አመልክተዋል።
በመድረኩ ከተገኙት የነዳጅ ማደያ ባለቤቶች መካከል አቶ ፎዚ ያህያ እንደተናገሩት፤ አላስፈላጊ ጥቅም ለማግኘት ሲባል የሚከናወነውን ህገ-ወጥ የነዳጅ ግብይት የመከላከሉን ተግባር እንደሚያጠናክሩም ተናግረዋል።
ሌላው ተሳታፊ አቶ አብዱሽኩር ጃሚ በበኩላቸው፤ አሰራርን መሰረት ያደረገ የግብይት ስርዓትን እንደሚከተሉና ይህንንም ከቢሮው ጋር በመቀናጀት እንደሚተገብሩት አመልክተዋል።